ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ከከተሞች ምስረታ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል

ሸገር ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ) ፦ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከከተሞች ምስረታ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ባከናወናቸው ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑ ተገለጸ።

የሸገር ከተማ የገበሬዎች ቀን "የገበሬው እና የዘመናዊ ከተማ ግብርና፡ ለአጠቃላይ ብልፅግና" በሚል መሪ ቃል በሱሉልታ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች እየተከበረ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም በከተሞች መስፋፋት እና እድገት ምክንያት በከተሞች ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተጎጂ ሆነው ቆይተዋል።

በመደመር እሳቤው ግን የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ከተሞች የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ባከናወኑት ሥራ አበረታች ለውጦች ተመዝግበዋል።


 

የሸገር ከተማም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ አርሶ አደሩን ያካተተ እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራ ያለ ሲሆን፣ በርካታ ለውጦችም እየተመዘገቡ መጥተዋል።

በዚሁ መሠረት በዛሬው ዕለት የሸገር ከተማ የገበሬዎች ቀን "የገበሬው እና የዘመናዊ ከተማ ግብርና፡ ለአጠቃላይ ብልፅግና" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች እየተከበረ ይገኛል።

አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ የባዛር እና ኤግዚቢሽን ፕሮግራም የተዘጋጀ ሲሆን፣ የግብርና ምርቶችም በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ይገኛሉ።


 

የዚህ መርሃግብር ዋነኛ ግብ ከተሞች በከተማ ግብርና በስፋት በመሰማራት በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር፣ ትኩስ የግብርና ምርቶችን በበቂ መጠንና በፍትሐዊ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ የኑሮ ውድነትን መቀነስ እና ገበያውን ማረጋጋት እንደሆነ ተገልጿል።

በመርሃግብሩ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) እና የኦሮሚያ ክልል ከተማ እና ቤት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ጉዮን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም