የክልሉን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል - ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል - ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን
አሶሳ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን ገለጹ።
የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን የታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅናና የታክስ ንቅናቄ መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን ግብር የሀገር ህልውና ማረጋገጫ እና የልማት ሥራዎች ማሳለጫ ሞተር መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የግብር አሰባሰብ ሂደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል ክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ወደ ሥራ በማስገባት የገቢ አቅምን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ በገቢ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማስተካከል መመሪያዎችን ከማሻሻል ጀምሮ የግብር ከፋዮችን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።
በክልሉ የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ልማትን በማፋጠን የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ገቢን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በተያዘው በጀት ዓመተም ከክልሉ የሚሰበሰበውን የገቢ አቅም አሟጦ በመሰብሰብ ትልልቅ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ከብልሹ አሰራር ለማላቀቅ እና ለማዘመን የሚያግዙ ዲጂታል አሰራሮችን መተግበር መጀመሩን ገልጸው፣ በተለይም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዘርፉ በስርዓት እንዲመራ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ተፈሪ አበበ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ክልሉ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት የገቢ ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ አሳክቷል።
ክልሉ በ2025 ዓ.ም የራሱን ወጪ በራሱ አቅም ለመሸፈን ማቀዱን ገልጸው፤ በተያዘው በጀት ዓመትም 15 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
በተመሳሳይ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና በታዩ ክፍተቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።