የግብፅ የውኃ አጠቃቀምና አያያዝ ለከፍተኛ ብክነት የተጋለጠ ነው -አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ - ኢዜአ አማርኛ
የግብፅ የውኃ አጠቃቀምና አያያዝ ለከፍተኛ ብክነት የተጋለጠ ነው -አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ የግብፅ የውኃ አጠቃቀምና አያያዝ ለከፍተኛ ብክነት የተጋለጠ መሆኑን የቀድሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ቡድን አባል እና የውኃ ሀብት ተመራማሪው አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ገለጹ።
አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ውኃዎች እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ (GERD) አማካሪ ቡድን ሰብሳቢ፣ እንዲሁም የምሥራቅ ናይል አህጉራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።
የውኃ ሀብት ተመራማሪው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ተራራማና ጥልቅ ሸለቆዎች ውኃን ለማከማቸት እጅግ ምቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ውኃን በእነዚህ ቀዝቃዛ አካባቢዎች ማከማቸት ለአባይ ተፋሰስ ሀገራት የሚጠቅም መሆኑንም አመልክተዋል።
ይህንን ሁኔታ በግብፅ ከሚገኘውና በበረሃማ አካባቢ በመገንባቱ ከፍተኛ የውኃ ትነት ከሚያጋጥመው የአስዋን ግድብ ጋር በማነጻጸር አቅርበውታል።
በአስዋን ግድብ በዓመት ብቻ ከ15 እስከ 16 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንደሚተንና እንደሚባክን ነው ያነሱት።
ውኃን በኢትዮጵያ ጥልቅ፤ ጠባብ ሸለቆዎች ውስጥ እና አመቺ የአየር ንብረት ባለበት አካባቢ ማከማቸት የትነት መጠንን ለመቀነስ እንደሚያስችልም አስረድተዋል።
ዋናው የውኃ ማከማቻ በኢትዮጵያ መሆኑ በሙቀት ሊባክን የሚችለውን በርካታ መጠን ያለው ውኃ ከማዳኑም በላይ፣ ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚለቀቀውን የውኃ መጠን አስተማማኝና የተረጋጋ እንዲሆን ያደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል።
እ.ኤ.አ በ2005 በግብፅ ከባድ የጎርፍ አደጋ በደረሰበት ወቅት የሀገሪቷ መሐንዲሶች 'ዌስተርን ስፒልዌይ' የተባለውን መስመር በመክፈት በቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚለካ ውኃ ወደ ቱሽካ ሸለቆ አቅጣጫ እንዲቀይር ማድረጋቸውን አውስተዋል።
ይህም የኢትዮጵያ ውኃ የማከማቸት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር በተፋሰሱ ላይ ያለውን ከመጠን ያለፈ የውኃ ብክነት ለመቀነስና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት መሠረተ ልማቶች ለጎርፍ አደጋ እንዳይጋለጡ ለመከላከል እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ተራራማ ሸለቆዎች የሚከማቸው ውኃ መጨመር በግብፅና ሱዳን በኩል በየዓመቱ የሚባክነውን አጠቃላይ የውኃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የውኃ ማከማቻዎች ጥቅም በውኃ ጥበቃ ብቻ የተወሰነ አለመሆኑንም የውኃ ሀብት ተመራማሪው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ከሀገር ውስጥ ፍላጎት አልፈው ንጹሕና በተመጣጣኝ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዲያገኙ የሚያስችል ዕድል እንደሚፈጥር ነው ያሉት።
እንዲህ ዓይነት የኢነርጂ ትብብር በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ላለው የኢኮኖሚ ትብብር ተጨማሪ አቅም እንደሆነም አንስተዋል።
ከእነዚህ ሁለገብ ጥቅሞች ተጠቃሚ ለመሆን በናይል ወንዝ ላይ በጋራ ተጠቃሚነትና መተማመን ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ትብብር ሊፈጠር እንደሚገባ አቶ ፈቅ አሳስበዋል።