ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሀገርና ለሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያስመሰከረ ነው -የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሀገርና ለሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያስመሰከረ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 15ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልና 18ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጉባኤው አባል የሃይማኖት ተቋማትን በማስተባበር አብሮነትን ለመገንባትና ሰላምን ለማጽናት አበረታች ተግባራትን አከናውኗል።

በሕዝቦች መካከል አንድነት፣ አጋርነትና ወዳጅነት ለመገንባት የተጀመረው ሀገራዊ ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ጉባኤው የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ጉባኤው ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ አባል የሃይማኖት ተቋማት ችግሮችን በጋራ በመፍታት በአብሮነት ታሪካዊ ድል መጻፋቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በዚህም ሊኮሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክርን ጨምሮ ሀገርን በሚመለከቱ አጀንዳዎች ላይ ጉባኤው ያበረከተው አስተዋጽኦ ለሀገርና ለሕዝብ አለኝታ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረ እንደሆነም ገልጸዋል።

ይህም አርአያ ከመሆኑም ባሻገር ለሌሎች መነሳሳትን የሚፈጥር ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

ጉባኤው ለበለጠ ውጤታማነት የመጣበትን ጉዞ በመገምገም ጥንካሬውን ማስቀጠል እንዳለበት ያመለከቱት ሚኒስትሩ፤ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ ደግሞ በጋራ መሥራቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር በትብብርና በአንድነት በመቆም መሥራት የሚገባበት ወቅት ነው።

ስለሆነም ከልዩነት ይልቅ በጋራ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለሰላም፣ ለእውነትና ለፍትሕ ምሳሌ የሆነ ማንነት መገንባት እንደሚገባ ጠቁመው፤ "ሕዝባችንን ከቃላችን በላይ በምግባራችን ልንመራ ይገባል" ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም