በአማራ ክልል የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው
ጎንደር፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና የሥርዓተ-ምግብ ችግርን በመቅረፍ ረገድ አበረታች ውጤት ማስገኘቱን የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ያለበትን ደረጃ እና በምርት አቅርቦት ረገድ እያስገኘ ያለውን ውጤት በጎንደር ከተማ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ሁነኛው በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የሥርዓተ-ምግብን ለማሻሻል የሌማት ትሩፋትን በስፋት የመተግበር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
መርሃ ግብሩ በቂ ምርት ለማቅረብ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የሚያስችል ውጤት ማስገኘቱንም ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመትም ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን በላይ እንቁላል፣ ከሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ቶን በላይ ወተት እና 900 ሺህ ቶን የሥጋ ምርት በማምረት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን በማሳያነት አንስተዋል።
በተጨማሪም ከ36 ሺህ ቶን በላይ ማር በማምረት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ጠቁመው፤ የዓሣ ልማቱንም በሐይቆች፣ በወንዞች እና በሰው ሠራሽ ኩሬዎች ጭምር በማስፋት አበረታች ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
ለሌማት ትሩፋት ማነቆ የነበረውን የመኖ እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍም 46 ዘመናዊ የመኖ ማቀናበሪያ ፋብሪካዎችን ወደ ማምረት ማስገባት መቻሉንም ጠቅሰዋል።
በከተሞችና አካባቢው በስፋት እየተካሄደ የሚገኘውን የሌማት ትሩፋት በቀጣይም በሁሉም የገጠር አካባቢዎች ለማስፋት የልምድ ልውውጥ እየተደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
በጎንደር ከተማ አስተዳደር እንስሳትና ዓሣ ሀብት መምሪያ የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ሀብታሙ ዘገዬ ፤ ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በየዘርፉ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።
በዘርፉ ተደራጅተው ወደ ሥራ ለገቡ ወጣቶች የብድር፣ የቦታ እና ሌሎች ድጋፎችን በመስጠት የከተማውን የእንቁላል፣ የወተትና የሥጋ አቅርቦት እጥረት በአጭር ጊዜ ማሻሻል መቻሉን አስረድተዋል።
ለመጪው የአዲስ ዓመት በዓልም ከ65 ሺህ በላይ የሥጋ ዶሮ፣ 40 ሺህ የደለበ በግና ፍየል በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በከተማው በዶሮና ንብ እርባታ የተሰማሩት ወይዘሮ ፅላተማርያም ተመስገን እንደተናገሩት፤ በ50 ጫጩቶች የጀመሩት የዶሮ እርባታ ሥራ ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓትም በሦስት ቅርንጫፎች 47 ሺህ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማራባት በቀን እስከ 27 ሺህ የሚደርስ እንቁላል ለገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ባደረገላቸው ድጋፍ የንብና የዓሣ ልማትን በተቀናጀ አግባብ መጀመራቸውን አመልክተው፤ በተሰማሩበት መስክም ለ137 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።
የ"ዘርፌ፣ ሀና እና ጓደኞቻቸው" ሽርክና ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽመልስ አርጋው በበኩላቸው፤ በ45 ሺህ ብር የጀመሩትን የወተት ልማት ስራ ላይ ጠንክረው በመሥራት ውጤታማ መሆን መቻላቸውን አመልክተዋል።