የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቃል ኪዳን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቃል ኪዳን
የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖዎች በአፍሪካ ላይ ማረፍ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ከተከታታይ የድርቅ ክስተቶች እስከ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋዎች አህጉሪቷን በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑም ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በእነዚህና በሌሎች ፈተናዎች ውስጥ የአፍሪካ አረንጓዴ ትራንስፎርሜሽን ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆና መጥታለች። በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎችን ከወረቀት አልፎ በተግባር በመከወን ስኬታማና ተጨባጭ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።
እ.አ.አ በ2011 ይፋ የሆነው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ከኢኮኖሚ እድገት ጎን ለጎን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር እና ከካርቦን ነጻ የሆነ ኢኮኖሚን የመገንባት ውጥን ያለው ነው።
ስትራቴጂውም አራት አንኳር ምሰሶዎች አሉት፦
የመጀመሪያው ዘላቂ ግብርና እና የቁም እንስሳት ውጤታማነትን ማሳደግ ሲሆን በዚህ ውስጥ ምርታማነትንና የአርሶ አደሮችን ገቢ መጨመር እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ብክለትን መቀነስ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
በደን ልማት አማካኝነት ለደኖች ጥበቃ ማድረግ፣ የደን መልሶ ልማት እና ካርቦንን አምቆ መያዝ የሚያስችሉ ግዙፍ አረንጓዴ ፕሮጀክቶችን ወደ ትግበራ ማስገባት ሁለተኛው ስትራቴጂካዊ ምሰሶ ነው።
የሃይድሮ፣ የእንፋሎት፣ የንፋስ እና የፀሐይ ታዳሽ ኃይሎችን ማስፋፋት ሌላኛው የትኩረት ማዕከል መሆኑ በስትራቴጂክ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
በትራንስፖርት፣ በኢንዱስትሪና በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ዘመናዊ እና ኃይል ቆጣቢ የቴክኖሎጂ አማራጮችን መጠቀም አራተኛው ጉዳይ ነው።
አረንጓዴ አሻራ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትልቁ የተግባር ማሳያ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ እስከ አሁን ከ54 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ስራ ማህበረሰብን በግልጽ በማሳተፍ በመተግበር ላይ የሚገኝ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው። ኢትዮጵያ የኃይል ምንጭ አማራጮቿን ከታዳሽ ኃይል እያገኘች መሆኗም የስትራቴጂውን ስኬታማነት ያመላክታል።
ብዝኃ የኢነርጂ አማራጮችን መጠቀም ከብክለት ነጻ የኃይል አቅርቦት እንዲገኝ እያደረገ ነው።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትውልድን የሚሻገር ሁሉን አቀፍ እሳቤ ሲሆን፤ ስትራቴጂው የኢኮኖሚ እድገትን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ያስተሳሰረና የብክለት ቅነሳን የሚያረጋግጥም ነው።
በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን ከመትከል እስከ የታዳሽ የኃይል ምንጭን ማስፋት የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት እመርታ በተግባር ገልጣ ማሳየት እያስቻላትም ይገኛል።