ሀገራዊ ምክክሩ በመደማመጥ ችግሮችን መፍታት እንደምንችል በተግባር ያረጋገጥንበት ነው- የጉባኤው ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ በመደማመጥ ችግሮችን መፍታት እንደምንችል በተግባር ያረጋገጥንበት ነው- የጉባኤው ተሳታፊዎች
ጎንደር ፤ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ) ፡-ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያዊያን በመደማመጥና በመመካከር ችግሮችን መፍታት እንደምንችል በተግባር ያረጋገጥንበት ነው ሲሉ የምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎች ገለጹ።
ሀገራዊ ምክክሩ ለመጀመሪያ ጊዜ አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሰባስቦ በመምከር አዲስ የታሪክ ምእራፍ የተከፈተበት መሆኑ ይታወቃል።
በዚሁ የምክክር ጉባኤ ህዝብን የወከሉ 4 ሺህ ተሳታፊዎች በምክክር ኮሚሽኑ በተለዩ ስምንት የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር በስኬት አጠናቀዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር የመዝጊያ ስነ ስርአት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፤ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ጥላ ስር በሀሳቦች ላይ በመምከር ችግሮችን በመፍታት ሀገር መገንባት እንደሚችሉ ያሳዩበት መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ ችግሮችን ከመፍታትም ባለፈ ለፖለቲካ ልምምድና የሀገር ግንባታ ጠንካራ መሰረት የሚያኖር መሆኑንም አንስተዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጉባኤው ተሳታፊዎች ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያዊያን በመደማመጥና በመመካከር ችግሮችን መፍታት እንደምንችል በተግባር ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ አባልና የምክክር ኮሚሽኑ የአማካሪ ኮሚቴ አባል አቶ ባዩ በዛብህ፤ የምክክሩ ሂደት ዜጎች ለሀገራቸው ዘላቂ ሰላምና እድገት በማሰብ በትኩረትና በጥልቀት የመከሩበት መሆኑን ገልጸዋል።
በጉዳዮች ላይ መመካከር ሲቻል ከሚነጣጠሉ ይልቅ የሚያቀራርቡ በርካታ የጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች እንዳሉ በተግባር የታየበት ስለመሆኑም አንስተዋል።
ሀገራዊ ተግዳሮቶችን በመሳሪያና በጉልበት ሳይሆን በሰለጠነ አግባብ በምክክር የመፍታት አዲስ ባህል የተፈጠረበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም አስረድተዋል።
ህብረተሰቡም የምክክሩን ውጤቶችና በምክክሩ የተደረሰባቸውን መደምደሚያዎች መሰረት በማድረግ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን መቀበልና መተግበር እንደሚገባው አሳስበዋል።
ሌላኛው የምክክር ጉባኤው ተሳታፊ የነበሩት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ መምህርና የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናት አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሀቢብ ሰይድ፤ የምክክር ሂደቱ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ውጭ ድጋፍና ጣልቃ ገብነት በራስ አቅም የተካሄደ በመሆኑ ታሪካዊ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ምክክሩ ማንኛውም ተሳታፊ ያለ ምንም ተፅዕኖና ጫና ሀሳቡን በነፃነት ያራመደበት፣ በቀረቡ ሃሳቦች ላይ በነፃነት በመከራከር በሃሳብ የበላይነት በመተማመን የተካሄደ ነበር ብለዋል።
እንደ አጠቃላይ የምክክር ሂደቱ በዚህ ዘመን ግጭትና ጦርነት አስፈላጊ አለመሆኑንና በምክክር የትኛውንም ችግር መፍታት እንደሚቻል በተግባር የታየበት ስለመሆኑ አስረድተዋል።
በመሆኑም ከምክክሩ የተገኙ ውጤቶችን በቀጣይነት ተግባራዊ በማድረግ የሀገርን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት የሁላችንም አደራና ሃላፊነት ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።