ቀጥታ፡

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ሁለንተናዊ ተቋማዊ የሪፎርም እርምጃ በአርዓያነት የሚወሰድ አስደናቂ ተግባር ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25 /2018 (ኢዜአ)፦ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በራስ አቅም የወሰደው ሁለንተናዊ ተቋማዊ የሪፎርም እርምጃ  በአርዓያነት የሚወሰድ አስደናቂ ተግባር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የአገልግሎቱ የለውጥ እርምጃዎች የሥራ ውጤታማነትን ከማላቅ እስከ ለምግብነት የሚውሉ የልማት ሥራዎች ተሰናስለው የተተገበሩበት መሆኑን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን አስታውቀዋል።


 

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በራስ አቅም የወሰደውን ሁለንተናዊ ተቋማዊ የሪፎርም እርምጃ ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም በአገልግሎቱ ቅጥር ግቢ የተወሰዱ የተቋም ዕድሳት፣ በከተማ ግብርና የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተከናወኑ የዶሮና በግ እርባታ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የንብ ማነብና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው የዕፅዋት ልማት ሥራዎችን አድንቀዋል።

በጉብኝቱ ወቅትም የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በራስ አቅም የወሰደው ሁለንተናዊ ተቋማዊ የሪፎርም እርምጃ  በአርዓያነት የሚወሰድ አስደናቂ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።


 

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን ጉብኝቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ በአብዛኛው ከጎረቤትና ከሌሎች ሀገሮች የመጡ  ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ ስደተኞችን በመቀበል፣ መብትና ክብራቸውን በማስጠበቅ ከተቀባዩ ማኅበረሰብ ጋር በማስተሣሠር በልማት ዕድሎች ተጠቃሚ እያደረገች ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስደተኞችን የመቀበል ታሪካዊ እሴትም በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፣ በውጭ ግንኙነትና በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የተቋሙን አገልግሎት ለማዘመን በራስ አቅም የተከናወኑ የሪፎርም እርምጃዎችም ለስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች አገልግሎት የተሳለጠ የሥራ ከባቢ መፍጠር መቻሉን አንስተዋል።

የአገልግሎቱ የሪፎርም እርምጃም ከዋና መሥሪያ ቤት እና በስድስት ክልሎች የሚገኙ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እንዲሁም 25 መጠለያ ጣቢያዎች ድረስ የዘለቀ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተወሰዱ ተቋማዊ የሪፎርም እርምጃዎችም ከሕንፃ ዕድሳት ባሻገር በሰራተኛ አቅም ብቻ የተከናወኑ የዶሮና በግ እርባታ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የንብ ማነብና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው የዕፅዋት ልማት ሥራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የተቋሙ የሪፎርምና የሌማት ትሩፋት የልማት ሥራዎችም ምቹና አረንጓዴ የሥራ ከባቢን በመፍጠር የራስን አቅም ለተሻለ ውጤት መጠቀም እንደሚቻል መልዕክት ያስተላለፈ ተምሳሌታዊ ተግባር ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም አገልግሎቱን ከኪራይ ቤት በማስወጣት ጭምር ዘመናዊ አገልግሎት መስጠትና ምቹ የሥራ ከባቢ መፈጠሩን አስታውሰዋል።

ስደተኞችን በዲጂታል መታወቂያና በአገልግሎት መስጫ ምኅዳር ያለአንዳች መጨናነቅ በኦንላይን ቀጠሮ በውስን ደቂቃዎች ዘመናዊ አገልግሎት የሚሰጥበትን ምኅዳር በውስጥና በራስ አቅም መፍጠር እንደተቻለ አስረድተዋል።


 

የኢትዮጵያ ስደተኛ አያያዝ ታሪካዊና በየዘመኑ እየዘመነ የመጣ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በሀገር ውስጥ እንደ ኢትዮጵያውያን እኩል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በቀጣይም በማካተት ፍኖተ ካርታ ትግበራ የበለጠ የመፈጸም አቅምን ለማጠናከር እንደሚሰራ በማስገንዘብ፣ ዓለም አቀፍ ልማት አጋሮችም የሚያደርጉትን ድጋፍ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሐሰንና የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በአገልግሎቱ ቅጥር ግቢ የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም