የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በራስ ዐቅም እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ኢትዮጵያ አካታች ልማት እያረጋገጠች መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በራስ ዐቅም እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ኢትዮጵያ አካታች ልማት እያረጋገጠች መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25 /2018 (ኢዜአ)፦የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በራስ ዐቅም እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ኢትዮጵያ አካታች ልማት እያረጋገጠች መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ተገኝተው የተቋሙን የሪፎርም ስራዎች ተመልክተዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ የተከናወነው ሪፎርም የሥራ ቦታዎችን ከማሻሻል ባለፈ፣ የሥራ ባህልን፣ የአገልግሎት ጥራትንና ተቋማዊ ዐቅምን የሚያጎለብት አዎንታዊ ለውጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የአገልግሎቱ አመራሮች፣ ሠራተኞችና ስደተኞች በመቀናጀት በዋና መሥሪያ ቤቱ፣ በ6 ክልሎች በሚገኙ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና በ27 መጠለያ ጣቢያዎች ያከናወኑት ሥራ በራስ ዐቅም ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ ጥሩ ተሞክሮ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተለይም የመደመር መንግሥት የግብርና እመርታ ማሳያ የሆነውን የሌማት ትሩፋት በመጠቀም በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዶሮና እንስሳት እርባታ፣ በንብ ማነብና በተለያዩ የዕጽዋት ልማት ዘርፎች የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህ ስኬት ተቋማዊ ሪፎርም የሚለካው በተሻለ የሥራ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሚፈጥረው ምርታማነትና ውጤት ጭምር መሆኑን ያረጋገጠ እንደሆነም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ ስደተኞችን በመቀበል፣ መብትና ክብራቸውን በማስጠበቅ እንዲሁም ከተቀባዩ ማኅበረሰብ ጋር በማስተሣሠር በልማት ዕድሎች ተጠቃሚ እያደረገች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አክለውም ስደተኞቹ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ መሆናቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውን በእጅጉ እያሳደገው ይገኛል ብለዋል።
በራስ ዐቅም የሚመጣ ለውጥ የተቋምን ዐቅም እንደሚያጎለብትና ይህም የሀገርን ዐቅም እንደሚገነባ ጠቁመው፤ በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት የታየው ስኬታማ ጉዞ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።