ቀጥታ፡

አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የመዲናዋ የአመራር አባላት በቁርጠኝነት ሊተጉ ይገባል

አዲስ አበባ ፣ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፦አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የመዲናዋ የአመራር አባላት በቁርጠኝነት ሊተጉ እንደሚገባ ከንቲባ  አዳነች አቤቤ ገለጹ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ውይይት አጠናቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ማጠቃለያ ባስተላለፉት የሥራ መመሪያ፤ መዲናዋን የብልጽግና ተምሳሌት የሚያደርጉ ተጨባጭ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ፕሮጀክቶችን በጥራት፣ በፍጥነትና በተሻለ አቅም የመፈጸም ልምድ እየጎለበተ መሆኑን ገልጸው፤ በውጤታማ የሀብት አጠቃቀም የተመደበው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ በማዋል የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል ብለዋል።

የሙሉ ቀን ሥራ ባህል እየሆነ መምጣቱን በማንሳት፤ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመለወጥ ዜጎቸን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ገቢራዊ በማድረግ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።

በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በመንገድ፣ በጤና፣ ትምህርት፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ በወንዝ ዳርቻዎችና ኮሪደር ልማት ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎቸን ለማከናወን ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።

በመሆኑም አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የመዲናዋ የአመራር አባላት በቁርጠኝነት ሊተጉ ይገባል ብለዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው፤ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተያዙ ዕቅዶችን ለማሳካት የአመራር አባላት የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የለውጥ ርምጃዎችን መጀመር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ዲሞክራሲ ስርዓት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ እንዳሉት፣ህዝቡ በምርጫው የሰጠንን ተጨማሪ ዕድል በልማት ለመካስ ለቀጣይ ተልዕኮ ራሳችንን ማዘጋጀት ይገባናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም