የአማራ ክልል ሕዝብ ጽንፈኝነትን በመታገል በክልሉ በሁሉም መስኮች ውጤት እንዲመዘገብ እያደረገ ያለው ስራ የሚበረታታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ሕዝብ ጽንፈኝነትን በመታገል በክልሉ በሁሉም መስኮች ውጤት እንዲመዘገብ እያደረገ ያለው ስራ የሚበረታታ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25 /2018 (ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል ሕዝብ ጽንፈኝነትን በመታገል በክልሉ በሁሉም የልማት መስኮች ውጤት እንዲመዘገብ እያደረገ ያለው ስራ ምስጋና የሚቸረው ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የአማራ ክልል ሕዝብ ለሀገር አንድነት፣ ለሥርዓተ መንግሥት መከበር እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ዋጋ ሲከፍል የኖረ፣ አሁንም እየከፈለ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።
ችግር ቢኖር እንኳን በሕግ አግባብ እንዲፈታ የሚጠይቅ፣ ለሕግ መከበር ቅድሚያ የሚሰጥ እና ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር ቀናኢ የሆነ ሕዝብ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡ በ2018 በጀት ዓመት ጽንፈኝነትን መታገሉን ገልፀው፤ የጸጥታ ኀይሉ እንዲጠናከር፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሕዝቡ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ባለው ቀናኢ አስተሳሰብ ምርጫን በአግባቡ በማካሄድ የሚሆነውን እንደራሴ መምረጡን አንስተዋል።
በክልሉ በፈተና ውስጥ ሆኖም ከፍተኛ የሆነ ልማት እንዳለም ገልጸዋል።ክልሉ የብልጽግናን እሳቤ በአግባቡ እየተገበረ መሆኑንም አንስተዋል።የክልሉ ሕዝብ መንግሥት ለሚተገብራቸው ተግባራት ሁሉ ተባባሪ እንደሆነም ገልጸዋል።የክልሉ ሕዝብ ለሠራነው ሥራ ዕውቅና ይሰጠናል፤ችግሮች ሲኖሩ ደግሞ በግልጽ ይናገራል ነው ያሉት።
በነጠላ ትርክት እና በጽንፈኝነት ላይ የተመሠረተ፣በትናንት በደሎች ላይ የተቸነከረ ፣ የሴራ ትንታኔ ያለበት እና ተቋማትን የሚበላ የፖለቲካ አካሄድ ለሀገር እና ለሕዝብ እንደማይጠቅምም ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ እንደ ሀገር የጋራ አሻራ እና ታሪክ እንዲኖር እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።የጋራ ታሪክ እና አሻራ አስቦ መሥራት ሲቻል ጠንካራ ፓርቲ፣ ጠንካራ መንግሥት እና ጠንካራ ሀገር መፍጠር ይቻላል ብለዋል።
ጠንካራ ክልላዊ የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት ይጠበቃል ያሉት አቶ አደም የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁኔታውን መገምገም እና መረጃ ላይ የተመሠረተ የሕግ ማስከበር ሥራን መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የፌዴራል መንግሥት እና ብልጽግና ፓርቲ ክልሉ በሚፈልገው ጉዳይ ሁሉ ከጎኑ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።