ቀጥታ፡

በክልሉ የህዝቦችን አብሮነት በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም የማጽናት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳዕና፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕዝቦችን አብሮነትና የሰላም እሴቶች በማጎልበት ዘላቂ ሰላምን የማጽናት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።

"ዘላቂ ሰላማችን ለሁለንተናዊ ብልፅግናችን" በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ መንግስት ፀጥታ ምክር ቤት የተዘጋጀ ዓመታዊ ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ የህዝቦችን አብሮነት በማጠናከር የሰላም እሴት ግንባታን ለማጎልበት የተጀመረው ቅንጅታዊ ሥራ ይጠናከራል፡፡

ለዚህም የሰላምና ፀጥታ ማዕከላትን በማጠናከር ህገ ወጥነትን የመከላከል፣ ከፋፋይ አስተሳሰቦችን የማረምና ህግ የማስከበር ስራ ትኩረት እንደተሰጠውም ጠቁመዋል።

የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት አባላት የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራትን በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የጋራ ትብብር ያሻል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ማህበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ እንዳለበትና የዚህ ድምር ውጤት በዘላቂ ሰላም ላይ የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው፣ በክልሉ በተለያየ መንገድ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን ጭምር በመጠቀም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ህዝቡ ችግሮችን በመነጋገርና በመወያየት የመፍታት ባህሉን እያጎለበተ መምጣቱን ጠቁመዋል።

የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት አባላት በየአካባቢው ያሉ የሰላም እሴቶችን በመጠቀም ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸውም ገልፀዋል።


 

የክልሉ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ መልከፀዴቅ በሰጡት አስተያየት በክልሉ አብሮነትን በማጠናከር ሰላምን ለማጽናት በተሰሩ ሥራዎች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

የክልሉ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለዚህ ስኬት ከመንግሥት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱንና ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥልም ጠቁመዋል።

የክልሉ የባህል ሽማግሌዎች ፎረም ሰብሳቢ ዳኛ ሞላ በለጠ እንደገለፁት በክልሉ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሴቶችን ለማጠናከር እንሰራለን ብለዋል።

ባህላዊ የሽምግልና ስነ ሥርዓትን ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ለህዝቦች አንድነት መጠናከር ለማዋል የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑንና ተግባሩን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ አስረድተዋል።

በመርሐ ግብሩ የክልሉ፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር የፀጥታ ዘርፍ እንዲሁም የክልሉ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከፍተኛ አመራሮች፣ የምክር ቤቱ አባላት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የባህል ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም