በአማራ ክልል ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል
ባህርዳር፣ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል በተያዘው የመኸር ወቅት የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈን መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በ2018/19 የምርት ዘመን በምግብ ራስን ከመቻል ያለፈ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት እየተሰራ ነው።
በምርት ዘመኑ ከአምስት ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት የእንክብካቤ ስራ ማከናወን እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አጠቃላይ ከለማው መሬት ውስጥ ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘመናዊ ትራክተር በማረስ ማልማት መቻሉንም አመልክተዋል።
ከሶስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሬት ደግሞ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የለማ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩ ሰብሉን የማረም፣ የመኮትኮትና ከተባይና ከበሽታ በመከላከል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ለዚህ የምርት ዘመንም አምስት ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ዘመናዊ የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ 524 ሺህ ኩንታል የተለያየ ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉን አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት ያለው አፈጻጸም በምርት ዘመኑ ይገኛል ተብሎ የታቀደውን ከ205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ አጠቃላይ ምርት ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የወንበርማ ወረዳ አርሶ አደር ቸኮል ታደለ፤ አራት ሄክታር መሬታቸውን በኩታ ገጠም አስተራረስና በትራክተር በማረስ በቆሎና ስንዴ መዝራታቸውን ገልጸዋል።
በባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ በመታገዝ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓት ተጠቅመው ያለሙት ሰብል እድገቱና ቁመናው በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከሁለት ሄክታር በላይ መሬታቸውን በወቅቱ በዘር ሸፍነው እየተንከባከቡ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ በሰሜን ጎጃም ዞን የጎንጅ ቆለላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አለምነው ደሴ ናቸው።
እያለሙት ያለው ጤፍና የበቆሎ ሰብል በጥሩ ቁመና ላይ የሚገኝ በመሆኑ የተሻለ ምርት አገኛለሁ ብለው እየሰሩ መሆናቸውን ነው የጠቀሱት።
በ2017/2018 የምርት ዘመን በክልሉ ከለማው አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ከ188 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማምረት መቻሉን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።