በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጤና አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጤና አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶች ተመዝግበዋል
ወልቂጤ፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጤና አገልግሎቱን ለማጠናከር በተከናወኑ ተግባራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶች መመዝገባቸው የክልሉ የጤና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ጤና ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ላይ በወልቂጤ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በዚህ ወቅት እንዳሉት የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን በተደረገ ጥረት ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ውጤታማ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ተችሏል።
ይህም በወሊድ ወቅት የሚከሰቱ የእናቶችና የሕጻናት ሞትን በመቀነስ የእናቶችን በጤና ተቋማት የመውለድ ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በህብረተሰብ አቀፍ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አማካኝነትም ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫና የመከላከያ ሥራዎች በመሰራቱ የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል ብለዋል።
ህብረተሰቡን በማሳተፍ ወባማ በሆኑ አካባቢዎች የትንኝ መራቢያ ስፍራዎችን ከማፋሰስና ከማዳፈን ባለፈ የአጎበር አጠቃቀምን ለማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል።
በእዚህም በክልሉ የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት ለመከላከል ተችሏል ብለዋል።
በጤና ተቋማት መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ ቁሶችን በማሟላትና የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻል ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም አቶ ሳሙኤል አክለው ገልጸዋል።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በተከናወኑ ሥራዎችም ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውን ነው ያስታወቁት።
የጤና ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ የሕጻናትና የእናቶች ጤና አገልግሎት ሽፋንና ጥራት ለማሳደግ በልዩ ትኩረት በመሰራቱ በጤና ተቋም የማይወልዱ እናቶች የማይገኙባቸውን ቀበሌዎቸ ተፈጥረዋል ብለዋል።
ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው መድረክ ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ አመራሮች፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣ የሆስፒታልና የጤና ጣቢያ ሥራ ሃላፊዎች በመሳትፍ ላይ ናቸው።