ቀጥታ፡

ባህላዊ ጥበብ ለኢኮኖሚ እድገት- የእደ-ጥበብ ውጤቶች በሐረሪ ክልል

በሐረሪ ክልል ባለፉት ዓመታት የእደጥበብ ውጤቶች እንዲዳብሩና የህዝብ ተጠቃሚነት የበለጠ እንዲጎለብቱ በማስቻል ረገድ ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል።

የሀረሪ ክልል መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን የዕድገትና ብልፅግና መሠረቶች መካከል አንዱ በማድረግ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

በተለይም የሐረሪ ሕዝብ እደ ጥበብ ውጤት የሆነው እና በክልሉ በሰፊው የሚመረተው የሐረር የጌይ ሞኦት (አለላ ስፌት) ምርት በዓለም አቀፍ ምድብ የንግድ ምልክት (ብራንድ) ሆኖ መመዝገቡ የዘርፉ አንዱ ማሳያ ሆኗል።

​ይህ ታላቅ ምዕራፍ የአዕምሮአዊ ንብረት ባለቤትነትን ለማስጠበቅ እና የዓለም አቀፍ ንግድ ተሳትፎን ለማዳበር ከፍተኛ ፋይዳ አለው።


 

የአለላ ስፌት ምርት በዓለም አቀፍ ምድብ የንግድ ምልክት ምዝገባ ምስክር ወረቀት ማግኘቱ፤ ለቱሪዝም ዘርፍ ልማት እና በዘርፉ ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን የሚያስገኝ ነው።

​በእያንዳንዱ የሐረሪ ቤት ባህላዊ የአለላ ስፌት ምርቶች መኖራቸው ከስጦታ፣ ከቤት ውስጥ መገልገያነትና ከማስዋቢያነት አገልግሎታቸው ባሻገር የማንነትና የባህል የላቀ መገለጫ በመሆናቸው ጭምር ነው።

እነዚህ የእደ-ጥበብ ውጤቶች በዓለም አቀፍ ገበያ የብራንድ እውቅና ማግኘታቸው የሐረርን ባህል፣ እሴትና ማንነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ትልቅ በር የሚከፍት ነው።

​ይህም በሥራው የሚሳተፉ ዜጎች በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ገበያ የመሳተፍና ተጠቃሚ የመሆን እድላቸውን በእጅጉ እንደሚያሰፋውና የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ገቢ ከፍ ከማድረግ አንፃር የጎላ ሚና ይጫወታል።


 

​የመደመር መንግሥት ቅርሶቻችን የሀገር ኩራት እንዲሆኑ እና እደ-ጥበብ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን ሚና ይበልጥ ለማጎልበት የጀመረውን ሁለገብ ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም