ሕብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ልምዱን በማሳደግ አምራቹን ማበረታታት አለበት - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
ሕብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ልምዱን በማሳደግ አምራቹን ማበረታታት አለበት - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
ሃዋሳ፤ ነሐሴ 25/2018(ኢዜአ)፡-ሕብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ልምዱን በማሳዳግ በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ማበረታታት እንዳለበት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ''የኢትዮጵያን ይግዙ'' በሚል መሪ ሃሳብ በሀዋሳ ከተማ የተዘጋጀውን የንግድ አውደ ርዕይና ባዛር ከፈተዋል።
በንግድ አውደ ርዕዩና ባዛሩ የቀረቡ ምርቶችን ተዘዋውረው የተመለከቱ ርዕሰ መስተዳድሩ ህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህሉን እንዲያሳድግ ጠይቀዋል።
የንግድ ሳምንቱ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር አጋዥ መሆኑንም ገልጸዋል።
ማህበረሰቡ በአምራች ኢንዱስትሪ መስክ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለማገዝና የሀገር ኢኮኖሚን ለመደገፍ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመግዛትና የመጠቀም ልምዱን ማጎልበት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊዋ ወይዘሮ ሰላማዊት መኩሪያ በበኩላቸው እንዳሉት አውደ ርዕይና ባዛሩ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህልን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ አቅምን ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡
በአውደ ርዕዩና ባዛሩ ላይ ቁጥራቸው 168 የሚሆኑ አምራቾች፣ ነጋዴዎች፣ ዩኒየኖች፣ ላኪዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎችና በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ላይ የሚሳተፉ ማህበራት ጭምር መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም መጪዎቹን በዓላት ታሳቢ ያደረጉ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አውደ ርዕይና ባዛሩ ዘላቂ የገበያ ትስስር በመፍጠር በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአውደ ርዕይና ባዛሩ ላይ ምርታቸውን ካቀረቡት መካከል የሲዳማ ዶና ህብረት ሥራ ዩኒየን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገነነ ልኡልሰገድ የአትክልና ፍራፍሬ ምርቶችን ይዘው መቅረባቸውን ገልጸዋል።
ከ5ሺህ በላይ አባላት የሚሰበስቧቸውን ምርቶችን በተሻለ የገበያ አማራጭ በማቅረብ ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ የአባላቱን የገቢ አቅም እያሳደጉ መሆኑን ገልጸዋል።
"የኢትዮጵያን ይግዙ" የንግድ አውደ ርዕይና ባዛር የገበያ ትስስር የሚፈጥር ምቹ አጋጣሚ በመሆኑ የአካባቢውን ምርት በሚገባ ለማስተዋወቅ እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል።
የብራውን ፉድ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ተወካይ አቶ መርዕድ ጋሹ የንግድ አውደ ርዕይና ባዛሩ ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ የተሻለ የገበያ ትስስር እንደሚፈጥሩበት ገልጸዋል።
የንግድ አውደ ርዕዩና ባዘሩ እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚቆይ በስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል።