የምክክር ጉባዔው ኢትዮጵያ በህዝቦቿ አንድነት የምታሸንፍ ሀገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባዔው ኢትዮጵያ በህዝቦቿ አንድነት የምታሸንፍ ሀገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያ በህዝቦቿ አንድነት የምታሸንፍ ሀገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ነው ሲሉ በጉባዔው ላይ የተሳተፉ ተመካካሪዎች ገለጹ።
ጉባኤው የምክክር ባህልን ያዳበረና የሀገሪቷን የፖለቲካ ባህል ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ታሪካዊ ክስተት መሆኑንም ተናግረዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ተመካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ አሳታፊ፣ ግልጽና አካታች በሆነ መልኩ የተከናወነው፤ ኢትዮጵያውያን ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ያረጋገጡበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ጉዮ ዋሪዮ እንደተናገሩት፤ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የሀሳብ ልዩነቶችን በግጭትና ጠመንጃ ለመፍታት ይደረግ የነበረውን የታሪክ አዙሪት በመቀየር አዲስ የፖለቲካ ባህልን የገነባ ነው።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያውያን ያለምንም ገደብና ስጋት ለሀገራቸው ይበጃል ያሉትን ሀሳብ በነጻነት ማዋጣታቸውን ተናግረዋል።
ሂደቱም ኢትዮጵያውያን ተነጋግረውና ተማክረው የመግባባት ባህላቸውን በተግባር ያሳዩበት፣ እንዲሁም እርስ በእርስ የተማማሩበትና ሀገራቸውን ያወቁበት ነው ብለዋል።
በምክክሩ ሂደት ከውጭና ከውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በማድረግ ሂደቱን ለማስተጓጎል ቢሞክሩም በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት በስኬት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ገብሩ በርሄ በበኩላቸው፤ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ኢትዮጵያውያን በጋራ ሀሳብ ላይ እንዲሰባሰቡ ማስቻሉን ተናግረዋል።
አራት ሺህ የሚደርሱ ተሳታፊዎች በአንድ ቦታ ተሰብስበው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
ይህ የምክክር መድረክ "ትንሽዋ ኢትዮጵያ" ተብሎ ሊገለጽ የሚችልና የሀገሪቷን ብዝሃነት በአንድነት ያንጸባረቀ መሆኑንም አብራርተዋል።
ተሳታፊዎች ያለምንም ተጽዕኖና በሙሉ ፍላጎታቸው ምክር ሀሳቦችን ማቅረብ መቻላቸውን ተናግረዋል።
ጉባኤው ኢትዮጵያ በምክክር እና በህዝቦቿ አንድነት የምታሸንፍ ሀገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ መሐመድ ቦሩ በበኩላቸው፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያሳተፈና ሀሳቦቻቸውን በነጻነት እንዲያዋጡ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ኢትዮጵያ አሸንፋለች" ያሸነፈችበት ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
ይህ የጋራ ተሳትፎና የምክክር ሂደት ሀገሪቷን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግርና የአንድነቷን መሰረት የሚያጠናክር መሆኑን አመላክተዋል።
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በሂደቱ ንቁ ተሳትፎ በማድረጋቸውና የጋራ ሀሳብ በማንሸራሸራቸው ምክንያት የምክክር ሂደቱ ውጤታማ መሆኑና የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋገጠ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ጉባኤው ኢትዮጵያውያን ያለ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በጋራ አጀንዳዎች ላይ እንዲመክሩ በማድረግ ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የውክልና ጦርነትና የቪዲዮ ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ የነበሩ አካላት ኢትዮጵያውያን ተቀራርበው መመካከራቸው እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲመክሩና ሲነጋገሩ የማይፈቱት ችግር እንደሌለ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።