ቀጥታ፡

ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማጠናከር ትፈልጋለች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፦ ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማጠናከር እና ከአፍሪካ አህጉር ጋር ያላትን አጋርነት ለማስፋት ፍላጎት እንዳላት የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉአንግኬትኪኦ ገለጹ።

የታይላንድ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉአንግኬትኪኦ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።

ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ አዲስ አበባ በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በአፍሪካ መካከል ዋና የትስስር ድልድይ ሆና እየወጣች መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከታይላንድ ጋር የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላት ሀገር መሆኗን አንስተው፤ ሀገራቸው ይህንን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እና ሁለንተናዊ ትብብሯን ለማሳደግ እንደምትሠራ አስታውቀዋል።

በተለይም በኢንዱስትሪ ልማት እና በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ረገድ ያላትን መልካም የልማት ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

የጉብኝታቸው ዋና ዓላማም ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እና መቀመጫነቱ አዲስ አበባ ከሆነው የአፍሪካ ኅብረት ጋር ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሆነ አብራርተዋል።

በዚህም ታይላንድ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ለመክፈት መወሰኗን ጠቁመዋል፡፡

ሀገራቸው በአፍሪካ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ለማጠናከር እና አዲስ አበባን የመላው አህጉራዊ ግንኙነቷ ዋና ማዕከል ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ሀገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የልማት አጋርነት ለማሳደግ ያለመውን "የታይላንድ-አፍሪካ ተነሳሽነት" የተሰኘ መርሃ-ግብር በልዩ ትኩረት እየተገበረች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ የአፍሪካ አህጉር ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው፤ አሁን ላይ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ በደቡቡ የዓለም ክፍል (Global South) ውስጥ ጠንካራ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ድምፅ ሆና መውጣቷን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የደቡቡ የዓለም ክፍል በዓለም አቀፍ መድረክ ያለው ተጽዕኖ እንደሚያመላክት ጠቅሰው፤ የታይላንድ ዋና ዓላማም ከዚሁ እውነታ ጋር የተጣጣመ አህጉራዊ አጋርነት መገንባት መሆኑን ገልጸዋል።

ከነባርና ከአዳዲስ የአፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ በመሥራትም ቀደም ሲል ከተመዘገቡት ስኬቶች በላይ በርካታ የጋራ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚቻል እምነታቸውን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ የአሴአን (ASEAN) እና የአፍሪካ ዋና የትስስር ማዕከል መሆኗን የጠቆሙት ዲፕሎማቱ፤ ኢትዮጵያና ታይላንድ በአፍሪካ ኅብረትና በአሴአን መካከል ጠንካራ የትብብር ድልድይ በመገንባት ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ የሚደረጉ የጋራ ጉብኝቶችና ተደጋጋሚ ውይይቶች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ታይላንድ እና የአፍሪካ ሀገራት ሕግን መሠረት ያደረገውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለማስጠበቅ፣ ነፃ ንግድን ለማስቀጠል እና በዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) ሥር ያለውን የንግድ ሥርዓት ለማጠናከር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆንም ከዓለም አቀፍ የንግድ ሕጎች እና ኢኮኖሚ ጋር በንቃት እንድትሳተፍ የሚያበረታታ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም