ቀጥታ፡

በክልሉ በመንገድና ትራንስፖርት ልማት ዘርፍ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል

ወልቂጤ፣ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመንገድና ትራንስፖርት ልማት ዘርፍ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ አበረታችሥራዎች መከናወናቸውን የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ከክልሉ፣ ከዞኖችና እና ልዩ ወረዳ የመጡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በትራንስፖርትና መንገድ ልማት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ዛሬ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።


 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ መሀመድ ኑርዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ለትራንስፖርት እና ለመንገድ ልማት ሥራዎች በተሰጠ ትኩረት ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረገ አበረታች ውጤት ተገኝቷል። 

በተለይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዘርፉ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው ያመለከቱት።

በዘርፉ የተከናወኑ እነዚህ ተግባራት የሕዝብን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማቀላጠፍ ባለፈ ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት መጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም አስረድተዋል።

 በመናኸሪያዎች የኢ-ትኬቲንግ አሰራርና ሌሎች የሪፎርም ሥርአቶችን ከመዘርጋት ባለፈ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ጠንካራ ቁጥጥርና የህግ ማስከበር ሥራ መሰራቱ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።

​እንደ ቢሮ ሀላፊው ገለጻ በክልሉ የትራንስፖርት አቅርቦት እጥረት በነበረባቸው አካባቢዎች አዳዲስ የሕዝብ ትራንስፖርት ስምሪቶችን በማስጀመር የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ተችሏል።

የተቀናጀ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሠራሮች በመዘርጋታቸውም የትራፊክ አደጋን መቀነስ አስችሏል ብለዋል።

እንደ መሀመድ (ዶ/ር) ገለጻ ​በመንገድ መሰረተ ልማት አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ባለፈ የነበሩትን በመጠገንና ደረጃቸውን በማሻሻል የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ 52 የመንገድ ፕሮጀክቶች ለመገንባት መቻሉን ነው የገለጹት።

መንግስት አርሶ አደሩን፣ ባለሀብቱንና የአካባቢውን ተወላጆች በማስተባበር የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያከናውናቸው  ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። 


 

በብልጽግና ፓርቲ የጉራጌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ናስር ሃሰን በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ በህብረተሰብ ተሳትፎ የመንገድ ከፈታና የድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራዎች ተከናውነዋል። 

ለአገልግሎት የበቁት እነዚህ ፕሮጀክቶች ለዓመታት ከህዝብ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ማስቻላቸውን ተናግረዋል።

በመደመር መንግስት ህዝብን በማሳተፍ የሚሰሩ የልማት ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም