በጋምቤላ ክልል ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ኢንሼቲቭን ስኬታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት አስተዋጾ እንዲጠናከር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ኢንሼቲቭን ስኬታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት አስተዋጾ እንዲጠናከር ተጠየቀ
ጋምቤላ፤ ነሐሴ 25/ 2018 (ኢዜአ)፡-በጋምቤላ ክልል ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ኢንሼቲቭን ስኬታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ።
በብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ላይ ያተኮረ እና የዘርፉ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አድሮው ቱት በውይይት መድረኩ ላይ እንዳሉት መንግስት የግብርናን ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በተለይም የፍራፍሬ ልማት በገበያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ይህም የአርሶ አደሮችን ገቢ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ኢኒሼቲቭ በፍራፍሬ ልማት ዘርፍ የታለመውን ግብ ለማሳካት አበርክቶው የላቀ ነው ብለዋል።
ኢኒሼቲቩ በክልሉም ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ገልጸው፣ ስኬታማ እንዲሆንም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አብርሃም ኡቻላ በበኩላቸው በክልሉ ለአቮካዶ ልማት ምቹ ስነ-ምህዳር ባላቸው የጎደሬና የመንገሺ ወረዳዎች ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም መጀመሩን ተናግረዋል።
በነዚሁ ወረዳዎች የአቮካዶ ልማቱን በማስፋትና ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ምርታማቱን እንዲያሳድግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
መድረኩ በአቮካዶ ችግኝ ልማትና የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎችን ማጠናከር፣ የአቮካዶ የድህረ ምርት አያያዝና የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም የባለሙያዎችና የአርሶ አደሮችን ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ያተኮረ መሆኑ ታውቋል።