በሲዳማ ክልል የንግድ ሥርዓቱን ፍትሃዊነትና ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የንግድ ሥርዓቱን ፍትሃዊነትና ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ይጠናከራል
ሀዋሳ፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የንግድ ስርዓቱን ፍትሃዊነትና ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራ እንደሚጠናከር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው "የኢትዮጵያን ይግዙ" የንግድ ሳምንት ላይ ያተኮረ ውይይት በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት በክልሉ የንግድ ስርዓቱን ፍትሃዊነትና ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ይጠናከራል።
ለዚህም ህጋዊ አሰራሩን የማዘመን ተግባራትን በማስቀጠል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ለማጉላት ይሰራል ብለዋል።
በንግድ ሥርዓት ውስጥ የሚታየውን ህገወጥነት ከመከላከል ባለፈ ግብር ከፋዩን በማበረታታት በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት በቅንጅት እንደሚሰራም አመልክተዋል።
በዚህም የማምረት አቅምን በማጎልበት በክልሉ ያሉ አስመጪና ላኪዎችን ቁጥር የማሳደግ ሥራ በትኩረት እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሰላማዊት መኩሪያ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ የሚካሄደው የንግድ ሳምንት የሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ልምድን እያሳደገ መጥቷል።
በዚህም በኢንዱስትሪና በግብርና ምርት ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች፣ ዩኒየኖች፣ ማህበራትና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን የተፈጠረላቸውን የግብይት ሥርአት በመጠቀም ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የንግድ ሳምንት መጪዎቹን በዓላት ታሳቢ ያደረጉ ምርቶችን በማቅረብ ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ በክልሉ የኤክስፖርት ምርት ላይ ያተኮረና በጥናት የተደገፈ ውይይት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በዚህም ቡናን ጨምሮ በአቮካዶና በሌሎች የኤክስፖርት ምርቶች ላይ ያለውን አቅም በመለየት የንግድና ግብይት ስርአቱን የማሳለጥ ሥራ በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።
በመድረኩ በኤክስፖርት ምርት ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን "የኢትዮጵያን ይግዙ" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የንግድ አውደ ርዕይና ባዛርም ይከፈታል ተብሎ ይጠበቃል።