ቀጥታ፡

የማዕድን ሀብትን በዘላቂነት በማልማት እና በአግባቡ በማስተዳደር ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን

አሶሳ፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፡- የማዕድን ሀብትን በዘላቂነት ለማልማት እና በአግባቡ ለማስተዳደር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ በየደረጃው ከሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር የማዕድን ሀብትን በዘላቂነት ማልማት በሚቻልበት መስክ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻደሊ ሀሰን፤ የማዕድን ሀብት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደገፍና የውጭ ምንዛሬ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልሉ የማዕድን ሀብት በስፋት እየተመረተ ቢሆንም ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠርና ዘርፉን በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅትም የማዕድን ሀብትን በዘላቂነት ለማልማት እና በአግባቡ ለማስተዳደር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የጠቀሱት።

የወጡ ህጎችና አዋጆች በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመሆናቸው በአግባቡ መተግበር እንዳለባቸው ነው የጠቆሙት።


 

በመሆኑም ማዕድን የሚወጣባቸውን አካባቢዎች መልሶ በማልማት የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቱጃኒ አደም በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚገኙ የማዕድን ሀብቶችን ለይቶ በማልማት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የማዕድን ሀብት የግጭት መንስኤ እንዳይሆን የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በህግ አግባብ ብቻ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም