በክልሉ የመሬት ሀብት አስተዳደርን በማዘመን የሕዝብ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የመሬት ሀብት አስተዳደርን በማዘመን የሕዝብ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አርባ ምንጭ፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሬት ሀብት አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመን የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
የክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና በ2019 ዕቅድ ላይ የሚመክር መድረክ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንዳሉት በክልሉ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመን የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ተግባር እየተከናወነ ነው።
በዚህም የወል፣ የመንግስትና በተቋማት የተያዙ መሬቶችን ለይቶ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋልና ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ምዝገባ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግስት የከተማና የገጠር መሬት አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመን የዜጎች የመሬት ይዞታ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ባከናወናቸው ተግባራት ውጤት መመዝገቡንም ተናግረዋል፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱ በዲጂታል አሠራር በመታገዙ በዘርፉ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥነትና የመሬት ወረራን ለመቆጣጠር ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ሲሆን፤ የተጀመሩ ሥራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በክልሉ በ65 ወረዳዎች እየተካሄደ ያለውን የመሬት ምዝገባ በውጤተማነት ለማጠናቀቅ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ባለሙያው የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ሰብስቤ ቡናቤ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ ባሉ ወረዳዎች ቀደም ሲል በማኑዋል የነበረውን የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ወደ ሲስተም አሰራር መቀየር ተችሏል ብለዋል።
የመሬት ሀብትን በዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በመምራት ፍትሃዊ የመሬት አጠቃቀም ለማስፈንና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ጉባኤው በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ላይ ከመከረ በኋላ በተያዘው በጀት ዓመት ዕቅድ ላይም ተወያይቶ የጋራ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡