ቀጥታ፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በሥራና ክህሎት ዘርፍ ጠንካራ መሠረት ተጥሏል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በባለፉት አምስት ዓመታት በሥራና ክህሎት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ለቀጣይ የልማት ጉዞ ጠንካራ መሠረት መጣላቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ካሚል ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባለፋት አምስት ዓመታት በሥራና ዕድል ፈጠራ በክህሎትና ልማት እንዲሁም የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ዋና ዋና የልማት ስኬቶችን ልምዶችንና የወደፊት አቅጣጫዎቸን የሚገመግም የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ባለፉት አምስት ዓመታት የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናን ከዘመኑ አስተሳሰብና ከገበያ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም የሚያስችሉ መሠረታዊ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም የኢኮኖሚ ኮሪደሮችና የዞን ክፍፍሎችን መሠረት ያደረገ የሥልጠና ተቋማት አደረጃጀት በማካሄድ ከአካባቢው የኢኮኖሚ ሀብትና ከኢንዱስትሪ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማረጋገጥም በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻሽል ሕጋዊ ማዕቀፍ ከመዘርጋት ባለፈ ማህበራዊ ውይይትን፣ የሥራ ቦታ ደህንነትና ጤንነትን ያማከሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ለቀጣዩ የልማት ጉዞ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን ቀዳሚ ሚና ለማጠናከር የሥልጠና ሥርዓቱን ከኢንዱስትሪው ጋር ማጣጣም ዋነኛ ትኩረት መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ ረገድ የግሉ ዘርፍ በሥልጠና ዲዛይን፣ አፈጻጸምና ግምገማ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ የተጀመረውን 'ሴክተር ስኪል ኢኒሼቲቭ' ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ማሸጋገር ያስፈልጋል ብለዋል።

የዲጂታል ክህሎት ልማትም የቀጣይ ትኩረት መሆኑን ጠቁመው፤ የዲጂታል 2030 ስትራቴጂን ለማሳካት ዜጎችን በዲጂታል ክህሎት ማስታጠቅ የሚኒስቴሩ ቁልፍ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረውን የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ወደ 7 ሚሊዮን ለማሳደግና ከዚያም በላይ ለማስፋት እንደሚሠራ አመልክተዋል።

ኢንተርፕረነርሺፕን ማስፋትና የፈጠራ ሥራዎችን ማበረታታትም የቀጣይ አቅጣጫ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

የሥልጠና ተቋማትንም ከመንግሥት በጀት ጥገኝነት በማላቀቅ ጥራት ያለው ሥልጠናና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያካሂዱ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

የልማት ሁሉ ማዕከል ሰው በመሆኑ የሠራተኛውን ብቃት፣ ተነሳሽነት፣ ክብርና ደህንነት ማረጋገጥም የቀጣይ ሥራዎች ትኩረት እንደሚሆን አስታውቀዋል።

የአምስት ዓመቱ ስኬቶች የአንድ ተቋም ብቻ ውጤት ሳይሆኑ የክልል አመራሮች፣ የተጠሪ ተቋማት፣ ሠራተኞች፣ የማህበራዊ አጋር አካላት፣ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች አጋሮች የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በመድረኩ የ“Skill Ethiopia” ኤክስፖም ተዘጋጅቶ በሥራና ክህሎት ዘርፍ የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎችና ባለሙያዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ ዕድል ተፈጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም