ቀጥታ፡

የዘንድሮ የዝናብ ሥርጭት ለግብርናው ምቹ በመሆኑ አስፈላጊውን የሰብል እንክብካቤ እያደረግን ነው -አርሶ አደሮች

ጊምቢ፤ ነሐሴ 25/ 2018 (ኢዜአ)፦ በምእራብ ወለጋ ዞን የዘንድሮው የአየር ንብረት እና የዝናብ ስርጭት ለእርሻው ምቹ በመሆኑ አርሶ አደሮች ለሰብላቸው ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገለጹ።

ምዕራብ ወለጋ ዞን ለም መሬት፣ የተስማማ የአየር ንብረት እና ከፍተኛ የውሃ አማራጭ እንዲሁም  የግብርና እምቅ አቅም ካላቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። 

በዞኑ በዋናነት እንደ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ማሽላ እና ስንዴ ያሉ የሰብል አይነቶች በሰፊው የሚመረቱ ሲሆን፣ አካባቢው በከፍተኛ የቡና አምራችነቱም ይታወቃል። 

የዞኑ አርሶ አደሮችም ይኸን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የእርሻ ስራቸውን በሙሉ አቅም በመተግበር ላይ ይገኛሉ።

አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ እንደገለጹት የዘንድሮው የአየር ንብረት እና የዝናብ ስርጭት ለልማት ስራቸው ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ እና በቂ የግብዓት አቅርቦት በመኖሩም በዘር የሸፈኑትን ሰብላቸውን በመንከባከብ ላይ ይገኛሉ። 

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የጊምቢ ወረዳ አርሶ አደር ፍቃዱ ቃሲም፤ የዘንድሮው የዝናብ ስርጭት ለሰብል ልማት ሥራቸው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በዚህም በአንድ ሄክታር መሬት ላይ በቆሎና ሩዝ ማልማታቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ፣ የአየር ንብረቱ ለሰብሉ አስፈላጊውን እንክብካቤ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር አቶ ኤባ ኦልጂራ በበኩላቸው፣ አንድ ሄክታር ተኩል መሬት በበቆሎና በስንዴ ሰብል ማልማታቸውን ገልጸዋል።

የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ ስለቀረቡላቸው አስቀድመው በዘር የሸፈኑትን መሬት፣ አሁን እየጣለ ባለው ምቹ የዝናብ ሁኔታ ታግዘው አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የዘንድሮው የመኸር ወቅት ለሰብል ልማት ሥራ ምቹ በመሆኑ፣ የዘር ሥራቸውን በወቅቱ አጠናቀው እንክብካቤውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እያገዛቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ የላሎ አሳቢ ወረዳ አርሶ አደር ፋረዳ ኦሊቃ ናቸው።

በዚህም የተሻለ ምርት ለማግኘት ከግብርና ባለሙያዎች የሚያገኙትን ምክር በአግባቡ በመተግበር ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

‎የምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈይሳ ሐምቢሳ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በዞኑ 486ሺህ 836 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።

ልማቱ በአብዛኛው በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በዘር መሸፈኑን ጠቁመው፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስፈልጉ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችም በወቅቱ ለአርሶ አደሩ መቅረባቸውን ኃላፊው አንስተዋል።

በአጠቃላይ በዞኑ በተያዘው የመኸር እርሻ መርሃ ግብር ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።"

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም