የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሰላም ባለቤትነት የመዲናዋ ሰላምና ደኅንነት ይበልጥ እንዲጠናከር አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሰላም ባለቤትነት የመዲናዋ ሰላምና ደኅንነት ይበልጥ እንዲጠናከር አስችሏል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የሰላም ባለቤትነትና የጸጥታ ኃይሎችን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማጠናከር ሰላምና ደኅንነት ይበልጥ ማረጋገጥ መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀጣይ አምስት ዓመትና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ በየደረጃው ባሉ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ውይይት ተደርጎበት ዛሬ ይጠናቀቃል።
በአምስት ዓመቱ ዕቅድ በከተማ ግብርና፣ በቤቶች ግንባታ፣ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች ሰው ተኮር ሥራዎች የመዲናዋን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ተግባራት ለማከናወን የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ ይደረሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተቋማት ያለፈውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በሚገባ በመፈጸም ያሳዩትን ቁርጠኝነት በቀጣዮቹ ዓመታትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ግልጽና ሊያሰራ የሚችል ዕቅድ ነድፈው እንዲንቀሳቀሱ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የነዋሪዎችን የሰላም ባለቤትነትና የጸጥታ ኃይሎችን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማጠናከር የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት ይበልጥ ማጠናከር ተችሏል።
ሕዝቡን ያሳተፈ የጸጥታ ሥራ በማከናወን ሕገ ወጥ ተግባራትን የሚጠየፍ ማኅበረሰብ በመፍጠር መዲናዋ የሰላም ደሴት እንድትሆን ተደርጓል ብለዋል።
አዲስ አበባ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ለማስቻል የመዲናዋ የሰላም ሠራዊት አደረጃጀት ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ ለእያንዳንዱ ጸረ ሰላም እንቅስቃሴ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት የሚሰራበት አውድ ተፈጥሯል ብለዋል።
ወንጀል ፈጽመው ለማምለጥ የሚሞክሩ ኃይሎችን በቀላሉ ለመቆጣጠር ከሸገር ሲቲ አስተዳደር ጋር በቅንጅት በመሥራት ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ አደራ በላቀ ደረጃ ለመፈጸም የሰላም፣ የጸጥታና ደህንነት ሥራ ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በዚህም የወንጀል ምጣኔን መቀነስ፣ የዜጎችን የሰላም ባለቤትነት ሚና ማላቅ፣ ልዩነቶችን በንግግር የሚፈታ ማኅበረሰብ በመፍጠር በሰላም እሴት ግንባታ ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፣ የመሬት ወረራና ሕገ ወጥ ግንባታ እንዲሁም ሌሎች ወንጀሎችን በመቆጣጠር የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት መዲና የማድረግ ራዕይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።