የአዲስ አበባን የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅዶች በሚገባ በመተግበር የነዋሪዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል – የከተማ አስተዳደሩ ሥራ ኃላፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባን የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅዶች በሚገባ በመተግበር የነዋሪዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል – የከተማ አስተዳደሩ ሥራ ኃላፊዎች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባን የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅዶች በሚገባ በመተግበር የነዋሪዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ የከተማ አስተዳሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀጣይ አምስት ዓመትና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ በየደረጃው ባሉ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ውይይት ተደርጎበት ዛሬ ይጠናቀቃል።
በአምስት ዓመቱ ዕቅድ በከተማ ግብርና፣ በቤቶች ግንባታ፣ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች ሰው ተኮር ሥራዎች የመዲናዋን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ተግባራት ለማከናወን የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ ይደረሳል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተቋማት ያለፈውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በሚገባ በመፈጸም ያሳዩትን ቁርጠኝነት በቀጣዮቹ ዓመታትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ግልጽና ሊያሰራ የሚችል ዕቅድ ነድፈው እንዲንቀሳቀሱ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአዲስ አበባን የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ በመተግበር የነዋሪዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል።
የአዲስ አበባ ከተማ የንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ እንዳሉት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን የንግድ ሥርዓቱን የአገልግሎት ምኅዳር የሚያሳልጥ አሰራር ተዘርግቷል።
ከ95 በመቶ በላይ አገልግሎቶችን በዲጂታል እንዲሰጡ በማድረግ ለንግዱ ማኅበረሰብ ቀላልና ምቹ የሥራ ከባቢ ተፈጥሯል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከ2013 ዓ.ም. በኋላ 7 የገበያ ማዕከላትን መገንባታቸውን በመጥቀስ፤ የሰንበት ገበያዎችን ቁጥር ወደ 264 ማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ በመዲናዋ ዜጎችን የቤት ባለቤት ማድረግ የሚያስችሉ ውጤታማ የቤት ልማት ሥራዎች ተከናወነዋል ብለዋል።
መንግሥት የግሉን ዘርፍ ጭምር በማሳተፍ ባለፉት አምስት ዓመታት 496 ሺህ የሪል ስቴት ቤቶች እንዲገነቡ ማድረጉን ገልጸዋል።
በዚህም መንግሥት የግል አልሚዎች በተለያዩ የግንባታ ዓይነቶች በቤት ልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚያስችል ምቹ ምኅዳር ፈጥሯል ብለዋል።
የንግድ ቢሮ ኃላፊዋ ሀቢባ ሲራጅ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የንግዱን ማኅበረሰብ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በመፍታት ፍትሐዊ የንግድ ውድድር የሚሰፍንበት አውድ እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
በአምስት ዓመት ውስጥ 357 የእሁድ ቅዳሜ ገበያዎችን እንዲሁም የግብርና ምርቶችን በጥራት፣ በዓይነትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚችሉባቸውን የገበያ ማዕከላት ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል ብለዋል።
ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት የመዲናዋን ነዋሪዎች የቤት ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ የቤት ልማት ግቦች መያዛቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ዘመኑ የደረሰባቸውን የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት በየዓመቱ 100 ሺህ ቤቶች ለመገንባት ታቅዷል ብለዋል።