የሀረሪ ክልል ካቢኔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የሀረሪ ክልል ካቢኔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላለፈ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፦ የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።
መስተዳድር ምክር ቤት በቅድሚያ የተወያየው የሀረሪ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ድርጅታዊ መዋቅር እና የሰው ኃይል ፍላጎት በተመለከተ በቀረበ ረቂቅ ላይ ነው።
ረቂቁም የሀረሪ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት በአንድ ቦታ በማሰባሰብ፣ በማደራጀትና ዲጂታላይዝ በማድረግ ተገልጋዩ ላልተፈለገ እንግልትና ወጪ ሳይጋለጥ ተደራሽ፣ ግልፅ፣ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት እርካታን ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
መስተዳድር ምክር ቤቱም ድርጅታዊ መዋቅር ላይ በሰፊው ከመከረ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።
ካቢኔው በመቀጠል የተወያየው በሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ለከንቲባ ኮሚቴ ውሳኔ የቀረበ የአደረጃጀት ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ነው።
የአደረጃጀት ማሻሻያውም ማዘጋጃ ቤቱ በህግ የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችለውን አደረጃጀት በመፍጠር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ውጤታማ የሆኑ ተግባራትን እንዲያከናውን ለማስቻል መሆኑ ተገልጿል።
ካቢኔውም በማሻሻያው ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይት በማካሄድ ውሳኔ ማሳለፉም ተመላክቷል።