አስቶንቪላ ከአርሰናል ፡- የሳምንቱ ተጠባቂ የሊግ ፍልሚያ - ኢዜአ አማርኛ
አስቶንቪላ ከአርሰናል ፡- የሳምንቱ ተጠባቂ የሊግ ፍልሚያ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2018 (ኢዜአ)፦ ዛሬ ምሽት አራት ሰዓት ላይ አስቶንቪላ ከአርሰናል በቪላ ፓርክ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።
አስቶንቪላ በመጀመሪያ የሊግ ጨዋታው በብራይተን የ4 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።
ሻምፒዮኑ አርሰናል የዋንጫ ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞውን ኮቨንተሪ ሲቲን 3 ለ 0 በመርታት ጀምሯል።
አስቶንቪላ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ቁልፍ ተጫዋቾቹን ማጣቱ ስብስቡ ላይ መሳሳት ፈጥሯል።
ሞርጋን ሮጀርስ፣ ኦሊ ዋትኪንዝ፣ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ፣ ኤዝሪ ኮንሳ፣ ዩሪ ቲሊማንስ፣ ሉካስ ዲኝ እና ዶኒየል ማለን አስቶንቪላን የለቀቁ ተጫዋቾች ናቸው።
ኒኮላስ ጃክሰን፣ ሊኦን ጎሬትዝካ፣ አሮን ዋን-ቢሳካ፣ ማቴዎ ሩጌሪ አሌሃንድሮ ጋርናቾ (ውሰት ማንችስተር ዩናይትድ) ጨምሮ የተለያዩ ተጫዋቾችን በማስፈረም አቅሙን ለማጠናከር እየሰራ ነው።
አርሰናል በበኩሉ ብሩኖ ጉማሬሽ፣ ክሪስቶስ ዞሊስ፣ ኤዝሪ ኮንሳ፣ ፒዬሮ ሂንካፒዬ እና ኢላን ሜስሊየርን በማስፈረም ስብስቡን አጠናክሯል።
ክሪስቶስ ዞሊስ በመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታ መልካም እንቅስቃሴ አድርጓል።
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 54 የሊግ ጨዋታዎች መካከል አርሰናል 29ኙን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አስቶንቪላ 11 ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪ 14 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
አርሰናል በ54ቱ ጨዋታዎች ላይ 92 ግቦችን ሲያስቆጥር አስቶንቪላ በበኩሉ 48 ጎሎችን ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
ባለፉት አምስት የሊግ ግንኙነታቸው አርሰናል በሶስቱ ሲያሸንፍ አስቶንቪላ አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል።
ክለቦቹ ባለፈው የውድድር ዓመት ባደረጓቸው ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አርሰናል ሁለቱንም አሸንፏል።
ከዝውውር እንስቃሴዎችና ከወቅታዊ ብቃት አንጻር አርሰናል የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝቷል።
ተጋጣሚው አስቶንቪላ ከመጀመሪያ የሊግ ሽንፈቱ በኋላ በሜዳው የሚያደርገው ጨዋታ ጠንካራ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለው መልካም አጋጣሚ ነው።
የ39 ዓመቱ አውስትራሊያዊ ጃሬድ ጊሌት ተጠባቂውን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት እንዲመሩ ተመድበዋል።