ቀጥታ፡

የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚጠይቀውን የዲጂታል ክህሎት የታጠቀ ትውልድ ማፍራት እያስቻለ ነው - አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 24/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በኢትዮ-ኮደርስ የአምስት ሚሊየን ስልጠና መርሃ ግብር በዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት የበለፀገ የሰው ሃይል ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ  የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን ማቲዎስ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀጣይ አምስት ዓመትና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ በየደረጃው ባሉ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ውይይት እየተደረገበት ነው።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ባለፉት አምስት ዓመት በስትራቴጂክ ዕቅድ የመፈጸም ቁርጠኝነታቸውን በቀጣዮቹ ዓመታትም አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የወጣቶችን ተሳትፎና ፈጠራ ማበረታታት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

ባለፉት አምስት ዓመታትም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የመዲናዋ ዜጎችን የሥራ ዕድል በመፍጠር የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደተቻለ ገልጸዋል።

በዚህም የአዲስ አበባ ወጣቶች በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ አገልግሎትናበሌሎች ዘርፎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

በቀጣይም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አጫጭርና መካከለኛ ሥልጠና በመስጠት ለኢንተርፕራይዞች በቂ የገንዘብ ብድር አቅርቦት እንደሚመቻች አስረድተዋል።

የአዲስ አበባን የዓለም የዲፕሎማሲ ከተማነት የሚመጥንና ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ልህቀት የታጠቀ ወጣት የሰው ሃይል ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮ-ኮደርስ የአምስት ሚሊዮን ስልጠና መርሃ ግብር ይፋ በተደረገ ማግስት ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ወጣቶች የሥልጠናው ተካፋይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የመዲናዋ ዜጎች ስልጠና በመስጠት በየትኛውም የዓለም ጫፍ የበይነ መረብ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በዚህም የ21ኛው ክፍለ ዘመን የቴክኖሎጂና ዲጂታል ሥምሪት የሚጠይቀውን ዕውቀትና ክህሎት የተላበሰ ወጣት ለማፍራት የኮደርስ ሥልጠና ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ደሳለኝ ተረፈ በበኩላቸው፤ የአዲስ መሶብ አንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በተቋቋመ ማግስት የተገልጋዮችን እርካታ ከ99 በመቶ በላይ ማድረስ አስችሏል ብለዋል።

በመዲናዋ በ11 ማዕከላት 25 የአዲስ አበባና የፌዴራል ተቋማት 150 አገልግሎቶችን እየሰጡ መሆኑን ገልጸው፤ እስከ መስከረም ወር ተጨማሪ ማዕከላት ይገነባሉ ብለዋል።

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የአገልግሎት አሰጣጡን ከእርካታ ወደ አመኔታ የማሸጋገር ዕቅድ መያዙን በማንሳት፤ የመንግሥት አገልግሎቶችን በተለያዩ አማራጮች እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም