ቀጥታ፡

የአፍሪካ የሰላምና ደኅንነት መዋቅር አስቸኳይ ማሻሻያ ያስፈልገዋል - መሐመድ አሊ የሱፍ

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 24/2018 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ የሰላምና ደኅንነት መዋቅር በአስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ የሚመራ አስቸኳይ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐመድ አሊ የሱፍ ገለጹ።

የአፍሪካ ኅብረት 21ኛውን አህጉራዊ ልዩ የግጭት መከላከልና አፈታት ጉባዔ በአንጎላ መዲና ሉዋንዳ አካሂዷል።


 

የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐመድ አሊ ዩሱፍ በጉባዔው ላይ እንዳሉት፤ የአፍሪካ የሰላምና ደኅንነት መዋቅር በአህጉሪቷ እየተደቀኑ ካሉ ሥጋቶች አኳያ አስቸኳይ ማሻሻያ ያስፈልገዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ እየታዩ የመጡት ቀጣይነት ያላቸው ቀውሶች የአህጉሪቷ ዋነኛ የሰላምና ደኅንነት ሥጋቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሽብርተኝነት፣ የጽንፈኝነት ጥቃት፣ የባሕር ላይ ዝርፊያ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልና ስደተኞችን አላግባብ ማስተናገድ የመሳሰሉ ሥጋቶች የአፍሪካ ሀገራት የጋራ እርምጃ እንዲወስዱ የሚጠይቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሊቀ መንበሩ ግጭትን መከላከል የኅብረቱ ቀዳሚ ትኩረት መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

የተጠናከረ አህጉራዊ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት፣ የኅብረቱ ውሳኔዎችን በተሻለ ሁኔታ መተግበርና ለሰላም ማስከበር ሥራዎች ዘላቂ የገንዘብ ምንጭ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ለዚህም በአስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ የሚመራና የሚተዳደር የሰላም ፈንድ መኖሩ ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ያሉትን ጨምሮ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሽርክናዎች የአፍሪካን እውነታና ፍላጎት በሚያንጸባርቅ መልኩ መጠናከር እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኅብረቱ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦችና ቀጣናዊ ስልቶች በመከላከያ ዲፕሎማሲ ውስጥ ማዕከላዊ ሚና እንዳላቸው አጽንዖት ሰጥተዋል።

በሰላምና ደኅንነት ምክር ቤት፣ በኮሚሽኑ፣ በአባል ሀገራትና በቀጣናዊ ተቋማት መካከል ቀጣይነት ያለው ምክክር ማድረግም ለጋራ ምላሽ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

የአፍሪካ የሰላምና ደኅንነት ሥጋቶችን አንድም ሀገር ብቻዋን መጋፈጥ እንደማትችል የሚያስገነዘቡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ለዚህም የጋራ ሀብትን ማሰባሰብ፣ አጋርነትን ማጠናከርና በሰላምና ደኅንነት ጉዳይ የበለጠ የፓን-አፍሪካ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሕገ-መንግሥታዊ ያልሆነ የመንግሥት ለውጥ የአፍሪካ ኅብረት አጥብቆ የሚኮንነውና በፅናት የሚቀጥል ግልጽ አቋም መሆኑን አንስተዋል።

የኅብረቱ ልዩ ጉባዔም የአፍሪካን የሰላምና ደኅንነት ጉዳይ በጋራ በመረከብ የራሷን አቅም የምታጠናክርበት መድረክ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሊቀ መንበሩ በማጠቃለያ መልዕክታቸው፤ ይህ የረጅም ጊዜ ሥራ የማይታክት የፖለቲካ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።

ጉባዔው አፍሪካ የሰላምና ደኅንነቷን በጋራ በመረከብ የራሷን አቅም የምታጠናክርበት መፍትሔ አመላካች መድረክ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም