ቀጥታ፡

ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ለስራ እድል ፈጠራና ለሀገር ገጽታ ግንባታ አቅም ፈጥሯል

ሆሳዕና፤ ነሐሴ 24/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለሀገራዊ ገጽታ ግንባታ ትልቅ አቅም መፍጠሩን የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

መንግስት ከግብርና መር ልማት  በመውጣት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በብዝሃ ዘርፍ ላይ ለመገንባት የቀረጸው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ተጨባጭ ለውጦችን እያመጣ መሆኑን ምሁራን ገልጸዋል።

ለዚህም የኢኮኖሚ እቅዶቹን በአምስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ በማተኮር በግብርና ዘርፍ በሌማት ትሩፋት ትግበራ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት  ከውጭ ከማስገባት ወደ ላኪነት ሲሸጋገር የሌማት ትሩፋትም የቤተሰብን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ አድርጓል።

በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተኪ ምርቶችን ማምረትና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን   በማስፋፋት  ላይ  ውጤት አስገኝቷል።

በማዕድን ዘርፉ የኢንዱስትሪና የኮንስትራክሽን ማዕድናትን በስፋት በማውጣት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ ላይ ይገኛል። 

ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባትም የዲጂታል መሠረተ ልማትን ማስፋት እንዲሁም የስልጠና ፕሮግራሞችን  በማቅረብ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ለማስፋት  እየተሰራ ነው። 

የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ረገድ የተከናወኑ ተግባራትም የሀገርን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፉ አዲስ መነቃቃት ፈጥረዋል። 

በተለይም የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ያበረከተውን አቅም በተመለከተ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከምሁራኑ  መካከል በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር በረከት  አድማሱ እንዳሉት የኢትዮጵያ  የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እቅድ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና  በማስተዋወቅ  ሀገራዊ እድገቱን ከማፋጠን አልፎ  ለሀገር ገፅታ ግንባታ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።

ለዚህም ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ መሰራታቸውን ለአብነት ሲጠቅሱ ይህም   ለስራ እድል ፈጠራ  ከፍተኛ አቅም ማበርከቱን ተናግረዋል።

አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማትና ነባር መዳረሻዎች እድሳትም የቱሪስት ፍሰቱን መጨመሩ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን እንዳጎላው ጠቅሰዋል፡፡

በዩኒቨርስቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርት ራሄል ደጉ በበኩላቸው  በመደመር መንግስት እሳቤ የለሙ የቱሪዝም መስህቦች  ዘላቂ ሀገራዊ  እድገት እንዲመዘገብ አስችለዋል ብለዋል።

በተለይም የቱሪዝም ልማቶች ከኮሪደር ልማትና ከፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጋር መተሳሰራቸው ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ፣ የቱሪስት ፍሰት ለመጨመር እና ቆይታቸውን ለማራዘም እንዳስቻሉም  አስረድተዋል።

ይህም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠርና የሀገርን ገጽታ ለመቀየር ከፍተኛ አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም