የኢትዮጵያ የከተማና ገጠር አስደናቂ የልማት ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ተሞክሮ የሚሆን ተምሳሌታዊ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የከተማና ገጠር አስደናቂ የልማት ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ተሞክሮ የሚሆን ተምሳሌታዊ ተግባር ነው
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 24/2018 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ የከተማና ገጠር አስደናቂ የልማት ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ተሞክሮ የሚሆን ተምሳሌታዊ ተግባር መሆኑን የአህጉር አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ገለጹ።
በአፍሪካ ሕብረት ልማት ኤጀንሲ የግብርናና የገጠር ትራንስፎርሜሽን ዋና ፕሮግራም ባለሙያ ክሌመንት አድጆርሎሎ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በከተሞችና መሠረተ ልማት ግንባታ አስደናቂ ለውጥ አስመዝግባለች።
አዲስ አበባን ለመጀመሪያ ጊዜ ያዩት እ.ኤ.አ. በ1999 እንደነበር በማስታወስ አሁን ከተማዋ በአስደናቂ የለውጥ ስኬት ውስጥ እየተጓዘች መሆኗን ገልጸዋል።
የመዲናዋ የልማት ስኬትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ የበረራ መዳረሻዎች አዲስ አበባን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል በማድረግ ለቱሪዝምና አገልግሎት ዘርፍ ወሳኝ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የከተማና ገጠር አስደናቂ የልማት ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ተሞክሮ የሚሆን ተምሳሌታዊ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
በአጀንዳ 2063 የቀጣናዊ ስትራቴጂክ ትንተናና እውቀት ድጋፍ ሰጪ ሥርዓት ዲፓርትመንት ኃላፊ ፖል ጉቲጋ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የከተማ ልማት ኢንቨስትመንት አስደናቂ ውጤት አምጥቷል ብለዋል።
የአፍሪካ ከተሞችን ሁለንተናዊ ለውጥ በውጤታማ አፈፃጸም መምራት ከተቻለ የአህጉሪቷን ዕድገትና ብልፅግና በማሳለጥ የኢኮኖሚ መነቃቃትና አቅም በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከተሞቿን በማስዋብ የፈጠረችው ጠንካራ የከተሜነት ምቹ የኢንቨስትመንት አቅም ለአፍሪካ ሀገራት ከተሞች ጭምር በልምድና ተሞክሮነት የሚወሰድ አስደናቂ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ለከተማና ገጠር ውጤታማ ሽግግር በቀላል ዋጋ የማይተመን አካታች የልማት አቅጣጫ እንደሚሆን አንስተዋል።
በዑጋንዳ ግብርና፣ የእንስሳት ኢንዱስትሪና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር የምግብና የሥነ ምግብ ዋስትና ረዳት ኮሚሽነር አሌክስ ባምቦና በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለሁላችንም የሚተርፍ ነው ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም እየገነባች ለመሆኗ ማሳያ ነው ብለዋል።