በጅማ ከተማ የተደራጁት የቅዳሜ ገበያዎች የምርት ዋጋን በማረጋጋት ሸማቹን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ከተማ የተደራጁት የቅዳሜ ገበያዎች የምርት ዋጋን በማረጋጋት ሸማቹን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው
ጅማ ፤ነሐሴ 24/2018 (ኢዜአ)፡- በጅማ ከተማ በሰፊው ተደራጅተው ሥራ የጀመሩት የቅዳሜ ገበያዎች የሸቀጦችንና የምግብ እቃዎችን ዋጋ በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከቱ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
አላስፈላጊ የዋጋ ንረት ለመግታት እና አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ለመደገፍ መንግሥት በቀጥታ ከአምራቾች፣ ከገበሬዎች እና ከህብረት ሥራ ማህበራት ምርቶችን የሚያቀርቡ የቅዳሜ እና የእሁድ ገበያዎችን በተለያዩ ከተሞች እንዲስፋፉ የማድረግ አቅጣጫ አስቀምጦ ሲሰራ ቆይቷል።
የጅማ ከተማ አስተዳደርም የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እና የገበያ ስርዓቱን ለማረጋጋት የቅዳሜ ገበያዎችን በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች በሰፊው በማደራጀት ወደ ሥራ አስገብቷል።
እነዚህ ገበያዎች አምራቾችና የህብረት ሥራ ማህበራት ያለምንም ደላላ ጣልቃ ገብነት ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለሸማቹ እንዲያቀርቡ ዕድል ፈጥረዋል።
ይህም በከተማዋ የሚታየውን ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ በመቀነስ፣ ሸማቾች ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝና በፍትሐዊ ዋጋ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ አዎንታዊ ውጤት እያስገኘ ይገኛል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ያካፈሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ቀደም ሲል የቅዳሜ ገበያ በጥቂት ቦታዎች ብቻ ይካሄድ ስለነበር ከፍተኛ መጨናነቅና መገፋፋት ይፈጠር ነበር ብለዋል።
አሁን ላይ የገበያ ቦታዎቹ በሰፊው መደራጀታቸው ይህንን እንግልት ማስቀረቱን አስረድተዋል።
የጅማ ከተማ ነዋሪዋ አስማ መሀመድ የቅዳሜ ገበያው በየቀበሌያቸው በቅርበት በመደራጀቱ ያለምንም እንግልትና በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት መቻሏን ገልጻለች።
ልዩ የቅዳሜ ገበያው በከተማዋ የሚስተዋለውን የዋጋ ግሽበት በመግታትና ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ከሚሳ ሀይሉ ናቸው።
በዚሁ ገበያ ከመደበኛው የገበያ ዋጋ በቀነሰ ዋጋ መሸመት መቻላቸው ለህብረተሰቡ ትልቅ እፎይታ መፍጠሩንም አክለው ተናግረዋል።
በገበያው ውስጥ በፀጥታ አካላትና በከተማው ንግድ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች አማካኝነት ሰፊና ቀጣይነት ያለው ክትትል በመደረጉ ምክንያት ጥራታቸው የተጓደሉ ምርቶች ለህብረተሰቡ እንዳይቀርቡ ማስቻሉንም አቶ ከሚሳ ገልጸዋል።
ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች የሆኑት ወይዘሮ ደሜ ሀይሉ እና አቶ ሙሌ ተመስገን በበኩላቸው ልዩ የቅዳሜ ገበያ የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ቀላል እና የተረጋጋ እንዳደረገላቸው ይገልጻሉ።
ወጣት ስንታየሁ ምሳው እንዳለው የቅዳሜ ገበያው ለሸማቾች ከሚሰጠው እፎይታ ባሻገር ለአምራች ወጣቶችም ሰፊ የገበያ ትስስር ፈጥሯል።
የጅማ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ረውዳ ጀማል በከተማዋ ከዚህ ቀደም በዘጠኝ ቦታዎች ብቻ ተወስኖ የነበረውን ልዩ የቅዳሜ ገበያ በ10 ቀበሌዎች በማስፋት ቁጥሩን ወደ 29 ማድረስ መቻሉንተናግረዋል።
የገበያ ቦታዎቹ እንዲስፋፉ መደረጉ የህብረተሰቡን እንግልት ለመቀነስ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ታስቦ መሆኑንም ኃላፊዋ አስረድተዋል።
አክለውም ከከተማዋ ውጭ ከሚገቡ ምርቶች ጎን ለጎን ከአካባቢው አምራቾች ጋር ሰፊ የገበያ ትስስር መፈጠሩንና እንዲያመርቱም ተገቢው ማበረታቻ መደረጉን ገልጸዋል።
የቅዳሜ ገበያዎችን ቁጥር በማሳደግ ምርቶችን በቅርበትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ የማቅረብ ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ወይዘሮ ረውዳ ገልጸዋል።