በጋምቤላ ክልል ለአሳ አጥማጆች የተደረገው የግብአት ድጋፍ አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ለአሳ አጥማጆች የተደረገው የግብአት ድጋፍ አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው
ጋምቤላ፤ ነሐሴ 24/2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ለአሳ አጥማጆች የተደረገው የግብአት ድጋፍ አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡
በጋምቤላ ክልል የሚገኙት ታላላቅ ወንዞችና የውሃ አካላት ክልሉን በዓሳ ሀብት ከፍተኛ አቅም ካላቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ ያደርጉታል።
ክልሉ በዓመት በሺዎች ቶን የሚቆጠር ዓሳ የማምረት አቅም ቢኖረውም፣ ዘርፉ ለብዙ ዓመታት በባህላዊ የአሳ ማጥመድ ዘዴዎችና በግብአት እጥረት ምክንያት የሚገባውን ያህል ጥቅም ሳይሰጥ ቆይቷል።
በክልሉ የሚገኙ አሳ አጥማጆች ዘመናዊ የዓሳ ማጥመጃ መረቦች፣ የጀልባዎችና የበረዶ ሳጥን አቅርቦት እጥረት ስለነበረባቸው፣ እንዲሁም ከምርት በኋላ የሚባክነውን የዓሳ መጠን የመቀነስና የገበያ ትስስር የመፍጠር ክፍተቶች ነበሩባቸው።
ይህን ክፍተት ለመሙላት የጋምቤላ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።
ቢሮው ለአሳ አጥማጆችና ለተደራጁ ማህበራት የቁሳቁስና የግብአት ድጋፍ ከመስጠቱም በላይ፣ በዘመናዊ የዓሳ አመራረት፣ አያያዝ፣ ጥራት አጠባበቅና ጥበቃ ዙሪያ ተከታታይ የሙያና ቴክኒክ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል።
የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ክርምስ ሌሮ እንዳረጋገጡት፣ እነዚህ የተደረጉት የግብአት አቅርቦቶችና የሙያ ድጋፎች አሳ አጥማጆቹ አሰራራቸውን ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ እንዲያሸጋግሩ፣ የምርት መጠናቸውን እንዲጨምሩ እና የቤተሰቦቻቸውን ገቢ በማሻሻል የአካባቢውን ኢኮኖሚ እንዲያነቃቁ አስችለዋል።
በተለይም የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረጉ ዘርፉን በእውቀት በመምራት የአስጋሪዎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ማገዙን ገልጸዋል።
በክልሉ የአሳ ልማትን ውጤታማ ለማድረግ በወንዞች፡ በሃይቆችና ሰው ሰራሽ የውሃ አማራጮች ጭምር በመተግበር የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 5 ሺህ 970 ቶን አሳ ምርት ታቅዶ ከእቅድ በላይ 10 ሺህ 840 ቶን ማምረት መቻሉን ገልጸዋል።
የዓሳ ሃብት ልማቱን ለስራ እድል ፈጠራ ለማዋል በተደረገው ጥረትም በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች የዓሳ ማስገሪያ፡ ማቀናባሪያና የማጓጓዣ ግብዓቶች እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ ከሌማት ቱትሩፋት መርሃግብር ጋር አቀናጅቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በአኝዋሃ ዞን በአቦቦ ወረዳ የሪዮ ቤር ዓሳ አምራች ማህበር አባል ወጣት ዳክ ኡጉት፤ የዓሳ ማስገሪያና የትራንስፖርት ድጋፍ በማግኘታቸው የዓሳ ምርታቸውን በጥራትና በወቅቱ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ተናግሯል።
የዓሳ ምርታማነታቸውን በጥራትና በብዛት ለገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ የገለጸው ደግሞ ሌላው የማህበሩ አባል ወጣት ጆክ ኡፑቲ ነው።