ቀጥታ፡

የቀይ ባህር ደህንነት እና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ሚና

(በሙሴ መለሰ)

በቀይ ባሕርና በኤደን ባሕረ-ሰላጤ ቀጣናዊ ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ የሚኖራት ሚና ከፍተኛ ነው።

የኢትዮጵያ አብዛኛው ወጪና ገቢ ሸቀጦች በባህር በር በኩል የሚተላለፉ በመሆኑ፣ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ የሚከሰቱ የፀጥታ መደፍረሶች ወይም የሎጂስቲክስ መስተጓጎሎች በቀጥታ በሀገሪቱ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ላይ የራሱን ተጽዕኖ ማሳረፉ የማይቀር ነው።

በሆርሙዝ ሰርጥ የተከሰተውን የጸጥታ ቸግር ተከትሎ የተለያዩ የዓለም ሃገራት የቀይባህር መስመር ከባቤል ሜንደብ እስከ ስዊዝ ቦይ ድረስ ያለው ደህንነት አሳስቧቸዋል።

ይሄንን ስጋት ለማቃለልም ሆነ የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውን መነሻ በማድረግ አንዳንድ ሃገራት በቀጣናው ካሉ የባህር ተጋሪ መንግስታት ጋር በመሆን የመሰረቷቸውን የጦር ሰፈሮች ቢያጠናክሩም አሁንም ቀጣናው በባህር ላይ ውንብድና፣ በህገ-ወጥ ንግድና የሰዎች ዝውውር ወንጀል ለስጋት የተጋለጠ ሆኖ ይገኛል።

የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ከቀይ ባህር ደህንነት ጋር በቀጥታ የተሳሰረ መሆኑን በጽኑ የምታምነው ኢትዮጵያ፣ ድንበር ተሻጋሪ የፀጥታ ስጋቶችን ለመከላከል በሚደረጉ የባለብዙ ወገን ውይይቶች ላይ በመሳተፍ የበኩሏን አስተዋጽኦ ታበረክታለች።

በተለይም ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ የጦር መሳሪያ እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን እንዲሁም የባህር ላይ ወንጀሎችን በጋራ ለመመከት የቀጣናው ሀገራት የተቀናጀ ምላሽ እንዲኖራቸው ድጋፍ ታደርጋለች።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር ያላት መልክዐ ምድራዊ ትስስር እና የፀጥታ አጋርነት በቀይ ባህር ቀጣና መረጋጋት ውስጥ ወሳኝ ድርሻ አለው።

በቀጣናው የሚከሰቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች እና የጸጥታ ችግሮች በቀጥታ በሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ በመሆናቸው፣ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የትብብር አማራጭን ተከትላ እየሰራች ትገኛለች።

የአፍሪካ ቀንድና የቀይባሕር ደኅንነት ሊለያዩ የማይችሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛቷ፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋና በጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጧ በቀጣናው ትልቅ ድርሻ ያላት በመሆኑ፣ በሚደረጉ የማሪታይምና የደኅንነት ውይይቶች ላይ የምታደርገው ንቁ ተሳትፎ ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ አስፈላጊ ነው።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ሰፊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ተጽዕኖ በመጠቀም፣ ስትራቴጂያዊ የንግድ መስመሮችን ከስጋት ነፃ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑ በቅርቡ በናይሮቢ በተካሄደው ዓለም አቀፍ መድረክ በግልጽ ታይቷል።

በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው አምስተኛው የቀይ ባህርና የኤደን ባህረ ሰላጤ የባህር ላይ ህግ ማስከበር ውይይት (Maritime Law Enforcement Dialogue) ላይ፣ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አገራዊና ቀጣናዊ ጥቅሞችን የሚያስጠብቅ ተሳትፎ አድርጓል።

ይህም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና የኢኮኖሚ ትስስር ላይ ያላትን ሚና እና ባለቤትነት አሳይቷል።

ለኢትዮጵያ የባህር በር ደህንነት የህልውና ጉዳይ ነው። በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ተወካይ ካፒቴን ክብሩ መስፍን እንደገለጹት፣ የባሕር ላይ ሰላም መደፍረስ በቀጥታ የአገሪቱን ብሔራዊ ኢኮኖሚ ይነካል።

አብዛኛው የሀገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ በባህር ላይ የሚካሄድ በመሆኑ፣ በቀይ ባህር ላይ የሚከሰቱ የባሕር ላይ ውንብድናዎችና ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች የንግድ ፍሰቱን እንዳያስተጓጉሉ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ካፒቴን ክብሩ አክለውም፣ የመርከቦች መድን ዋስትና መናርና የሸቀጦች መዘግየት የሀገሪቱን የንግድ ተወዳዳሪነት እንዳይፈታተኑ፣ ጠንካራና የተቀናጀ የባህር ላይ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህን ዓለም አቀፋዊ ስጋትን ለመመከት ኢትዮጵያ የጋራ መፍትሔዎችን በማቅረብ ረገድ ግንባር ቀደም ናት። በተለይም ከጎረቤት አገራት ጋር በመቀናጀት "ብሔራዊ የማሪታይም መረጃ ማዕከል" (National Maritime Information Centre) ለመመስረት ያቀደችው ስትራቴጂ፣ ሀገሪቱ ለቀጣናው መረጋጋት ያላትን የረጅም ጊዜ ራዕይ የሚያሳይ ነው።

መረጃን በጋራ መለዋወጥና የተቀናጀ የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ ለዚህ ስኬት ዋነኛው መሳሪያ እንደሆነ ኢትዮጵያ በጽኑ ታምናለች።

በቀይ ባህርና በኤደን ባህረ-ሰላጤ የሚስተዋሉ እንደ ሕገ-ወጥ የሰዎችና የዕፅ ዝውውር እንዲሁም ሕገ-ወጥ አሳ ማጥመድ ያሉ ስጋቶች ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ቀጣናዊ ኃይሎች ተሳትፎ የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ትኩረት ስቧል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአደንዛዥ ዕፅና ወንጀል ጉዳዮች ቢሮ (UNODC) የቀጣናው አስተባባሪ ሞስታፋ ኤልባና እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላት የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቅም ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች አስተማማኝና የተረጋጉ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

በቀይ ባህር ቀጣና ያላትን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስጠበቅና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአደንዛዥ ዕፅና ወንጀል ጉዳዮች ቢሮ (UNODC) ኢንተርፖል እና ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በቅርበት በመሥራት ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና ጸጥታ ላይ ያላትን የመሪነት ሚና በታሪካዊ ኃላፊነትና በሕግ አግባብ እያስጠበቀች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ የባህር ሃይልን ጨምሮ በጥብቅ ዲሲፕሊኑ እና በመፈጸም አቅሙ የሚታወቅ ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት ገንብታለች።

ይሄ ሰራዊት በተለያየ ጊዜ ችግር ላጋጠማቸው ሃገራት ባሳየው የሰላም ማስከበር ሚናው በውጤታማነቱ የተመሰከረለትም ነው።

የቀጣናውን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ሃይል አስፈላጊ ስለሆነም በቅርብም በሩቅም ያሉ ሃገራት የኢትዮጵያን የባህር ላይ ህልውና በበጎ ይመለከቱታል።

ለዚህም በቅርቡ በአንድ የሃገር ውስጥ ሚዲያ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ የባብኤል ሜንደብን እና የቀጣናውን ሰላም ለማስጠበቅ ሃገራቸው በቂ አቅም ስለሌላት የሌሎች እገዛ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት የጅቡቲ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ፋይናስ ሚኒስትር ኢሊያስ ሙሳ ዳዋሌህ ገለጻ አንዱ ማሳያ ነው።

እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች አመላካች የሚሆኑት ያለ አግባብ ከባህሩ የተገፋችውና መብቷን የምትጠይቀው ኢትዮጵያ ያላት ዘርፈ ብዙ ዓቅም ለቀጣናውም ለራሷም ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ወሳኝ ሚና ያላት መሆኑን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም