ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ጎረቤት ሀገራት በአግባቡ ሊረዱት የሚገባ መሠረታዊ ጉዳይ ነው - የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፑዋንግኬትኬው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፤ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ጎረቤት ሀገራት በአግባቡ ሊረዱት የሚገባ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፑዋንግኬትኬው ገለጹ።

ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥርና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አንጻር የባሕር በር የማግኘት ጉዳይን የህልውና አጀንዳ አድርጋ እየሰራች ትገኛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀጣናው ግዙፍ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና መቀጠል እንደማትችል በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ይህንን ጥያቄዋን በንግድና ሰጥቶ መቀበል መርህ ለማሳካት በቀጣይነት እንደምትሰራም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መናገራቸው አይዘነጋም።

በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፑዋንግኬትኬው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የባሕር ወደቦች ለአንድ ሀገር ንግድና ኢንቨስትመንት እጅግ ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ጎረቤት ሀገራት በአግባቡ ሊረዱት የሚገባ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የባሕር በር የማግኘት ሂደቱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጋራ ጥቅምና ዕድገትን መሰረት ባደረገ መልኩ ሊከናወን እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል ሊኖር ከሚገባው የትብብር ማዕቀፍ ጋር የሚተሳሰር መሆኑንም ነው ያነሱት።

በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ድምፃቸውና ፍላጎታቸው ተሰሚነት እንዲያገኝ በጋራና በትብብር መስራት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም የደቡብ ንፍቀ ክበብ ሀገራት በዓለም አቀፉ ሥርዓት ውስጥ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትብብር መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ አፍሪካ ለዚህ ትብብር ዋነኛዋ ድምጽ ሆና እየወጣች ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን አፍሪካን ከኢስያ አህጉር ጋር በማስተሳሰር ረገድ መግቢያ በር ሆና እያገለገለች እንደምትገኝም የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፑዋንግኬትኬው ተናግረዋል።

ትብብርን እና በሕግ ላይ የተመሠረተውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለማስጠበቅ ተመሳሳይ አመለካከት ባላቸው ሀገራት መካከል የበለጠ ወዳጅነት እና አንድነት እንዲኖርም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም