በአማራ ክልል በፍትህ ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በፍትህ ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው
ባህር ዳር፤ ነሃሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በፍትህ ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከፍተኛ አመራሮች በአማራ ክልል የሚገኙ የፍትህ ተቋማትን የሪፎርም አተገባበር ጎብኝተዋል።
ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ በፍትህ ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት ዘመኑን የዋጁ አስደናቂ ስራዎች ናቸው ብለዋል።
በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተተገበረው በዲጂታል የተደገፈ የኢ-ፋይል አሰራር ፍትሃዊ፣ ግልጽና የተገልጋዩን እንግልት መቀነስ ያስቻለ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
ተገልጋዮች ጉዳያቸውን ባሉበት ሆነው በበይነ መረብ በመከታተል አስተማማኝ ፍትህ እንዲያገኙ መደረጉ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል የተሄደበትን ርቀት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያም ምቹ የስራ አካባቢን በመፍጠርና የዲጂታላይዜሽን አሰራርን እውን በማድረግ የተሰራው ስራ አበረታች መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
በቴክኖሎጂ የዳበረ የፍትህ ስርዓት ለማስፈን በተሰራው ስራ የአመራሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን መገንዘባቸውን ጠቁመው፤ በጉብኝታቸው ትልቅ ተሞክሮ ማግኘታቸውን አረጋግጠዋል።
በቀጣይ በመተጋገዝና በአብሮነት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከክልሉ የፍትህ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን በበኩላቸው የዳኝነት ስራ ከፖሊስ የወንጀል መከላከልና የተጠናከረ ምርመራ ተግባር ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዲጂታላይዜሽን ትግበራ ቀልጣፋና ፍትሃዊ የፍትህ አሰጣጥ እንዲኖር ያስቻለ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም ከከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ለይግባኝ ይመጡ የነበሩ ባለጉዳዮች ባሉበት ቦታ ሆነው ጉዳያቸውን በመከታተል ገንዘብንና ጉልበታቸውን እንዲቆጥቡ አስችሏል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከፍተኛ አመራሮች ያደረጉት ጉብኝት ልምድ ከመለዋወጥ ባሻገር ተግባራትን በትብብር ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የሪፎርም ትግበራውን እስከ ታች ድረስ ለማውረድ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በጉብኝቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አመራሮች ተገኝተዋል።