በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ግብዓቶችን በማሟላት ቀጣዩን የምህርት ዘመን ስኬታማ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ግብዓቶችን በማሟላት ቀጣዩን የምህርት ዘመን ስኬታማ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል
ወልቂጤ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ግብዓቶችን በማሟላት ቀጣዩን የምህርት ዘመን ስኬታማ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በጉራጌ ዞን በህብረተረብ ተሳትፎ የታተሙ ከ160 ሺህ በላይ መጽህፍትን በዞኑ ለሚገኙ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች አስረክበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት በቅድመ-መደበኛ ትምህርት ላይ መስራት ተማሪዎች ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል።
በመሆኑም ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው፤ ግብዓቶችን በማሟላት የ2019 የትምህርት ዘመንን ስኬታማ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።
እንደሀገር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተያዘውን አቅጣጫ ውጤታማ እንዲሆን ዘርፉን የመደገፍ ሥራ በትኩረት እንደሚከናወንም አመልክትዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በበኩላቸው፤ በክልሉ ለ2019 የትምህርት ዘመን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም በክልሉ ላሉ ቅድመ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ መጽሃፍት መሰራጨታቸውንም በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
በህብረተሰብ ተሳትፎ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የመገንባትና ደረጃቸውን የማሻሻል ሥራ መከናወኑንም አመልክተዋል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በዞኑ ለቅድመ አንደኛ፣ ለአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 160ሺህ 169 መጽሃፍት መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።
መጽሃፍቱ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የታተሙ ሲሆን ከ37 ሚሊዮን ብር በላይም ውጪ የተደረገባቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በህዝብ ተሳትፎ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ለመማር ማስተማር ሥራው ዝግጁ መደረጋቸውን ተናግረዋል።