የሀዋሳ ከተማን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚመጥኑ ውጤታማ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ከንቲባ ጥራቱ በየነ - ኢዜአ አማርኛ
የሀዋሳ ከተማን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚመጥኑ ውጤታማ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ከንቲባ ጥራቱ በየነ
ሀዋሳ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ የሀዋሳ ከተማን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚመጥኑ ውጤታማ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማዋ ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለፁ።
በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት "ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ የጽዱ ኢትዮጵያ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ከንቲባ ጥራቱ በየነ፤ የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚመጥኑና ከተማዋን ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የሚያግዙ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።
በከተማዋ ከኮሪደር ልማት ሥራ ጋር በተያያዘ ሰፋፊ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እንዲሁም በየአካባቢው የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች መገንባታቸውንም አመልክተዋል፡፡
ሃዋሳ ውበትና ጽዳት መለያዋ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባ ጥራቱ፤ ከከተማዋ ዕድገትና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ላይ ውስንነቶች እንዳሉ ተናግረዋል።
ይህንን ችግር ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በ2019 ዓ.ም የከተማዋን አድገት የሚመጥን አዲስ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት ጋር ተጣጥመው እየተከናወኑ ያሉ ውጤታማ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
የሃዋሳ ከተማ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሹምባሻ በበኩላቸው በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ከአካባቢ ጥበቃ ሥራ ጋር የተሰናሰለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ በየመንደሩ ቆሻሻ የሚሰበስቡና ለይተው የሚያስወግዱ ማህበራትን በማደራጀት ጽዱ አካባቢን የመፍጠር ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡