ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች የሐረር ከተማን የቱሪዝም መዳረሻነት እያሳደጉ ነው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ) ፦ በሐረሪ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የሐረር ከተማን የቱሪዝም መዳረሻነት በማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እያስገኙ መሆናቸውን የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሚ አብዱልዋሲ ገለጹ።

መንግሥት ካለፉት ዓመታት ወዲህ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን በመግለጥ፣ በርካታ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና ለነባሮቹም እሴት የሚጨምሩ ተግባራትን በማከናወን የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻነት እያሳደገ ይገኛል።


 

የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሚ አብዱልዋሲ እንደገለጹት፤ የክልሉን እምቅ የቱሪዝም ሃብት አልምቶ በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ነው።

በተለይም በመደመር መንግስት ቱሪዝም ከዋና የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ አንዱ ሆኖ መወሰዱና ትኩረት መሰጠቱ ዘላቂነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ገልፀዋል።

በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክልሉ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ከማልማት ባሻገር ነባር ቅርሶችን በመጠገንና በመንከባከብ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በጁገል አለም አቀፍ ቅርስ እድሳትን ጨምሮ ነባርና አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎችና መሰል ተግባራት የክልሉ ቱሪዝም በፍጥነት እንዲነቃቃ እያደረገ መሆኑንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሃገራት ጎብኚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በክልሉ የቱሪስት መስህብ ሃብቶችን የማስተዋወቅ፣ መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማትና መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም