የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማደግና ዲጂታላይዜሽን የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ እያሻሻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማደግና ዲጂታላይዜሽን የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ እያሻሻለ ነው
ቦንጋ ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማደግና ዲጂታላይዜሽን የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ እያሻሻለ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የቦንጋ ከተማ ነዋሪ ምሁራን ገለጹ።
የመደመር መንግሥት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠንና አገልግሎቶችን ለማዘመን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በተግባር ማየታቸውንም ምሁራኑ ተናግረዋል።
የኮሌጁ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምህር ምስጋናው ታደሰ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የዲጂታላይዜሽን ትግበራ የሀገር ልማትን ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ የመንግሥት አሠራር ብቃትን ማሳደጊያ እና የዜጎችን ኑሮ ማሻሻያ መሣሪያ ነው።
የመደመር መንግሥት ለዲጂታላይዜሽን በሰጠው ልዩ ትኩረት ውስጥ ተግባራዊ የተደረገው የዲጂታል 2025 እስትራቴጂ የዜጎችን የአኗኗር ሁኔታ በተጨባጭ ማሻሻሉንም ነው ምሁሩ የተናገሩት።
በዚህ እስትራቴጂ በሞባይል ባንኪንግ፣ በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በኦንላይን አገልግሎቶችና በዲጂታል መታወቂያ ዘርፎች የተመዘገቡ ለውጦች ዜጎች የተለያዩ አገልግሎቶችን በቀላሉና በተፋጠነ መንገድ እንዲያገኙ ያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍም አዳዲስ የንግድ ዕድሎችን የፈጠረ ሲሆን የዚሁ አካል የሆነው የ‘ኢትዮ-ኮደርስ’ ፕሮግራም ወጣቶችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ከመሆን ባለፈ የቴክኖሎጂ ፈጣሪ እንዲሆኑ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
በመሆኑም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተገኙ አበረታች ውጤቶች ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ጠንካራ መሠረት የጣሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተከናወኑት ተግባራት ዲጂታል ኢኮኖሚውን በማስፋፋት የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሻሻላቸውን የገለጹት ደግሞ የኮሌጁ የመረጃ ቴክኖሎጂ መምህር ታደሰ ዘውዴ ናቸው።
ከዚህ ውስጥም የ‘መሶብ’ የአንድ ማዕከል አሠራር የመንግሥት አገልግሎቶችን ተደራሽነት በማሻሻል ዜጎች ጊዜና ወጪያቸውን በቆጠበ መልኩ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያደረገ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል።
የዲጂታል 2025 መጠናቀቅን ተከትሎ የተተገበረው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በኢኮኖሚው ዘርፍና በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰፊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑንም ነው የገለጹት።