ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግማሽ ፍጻሜው ሽንፈት አስተናገደ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ 3 ለ 0 ተሸንፏል።

በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጆቪያ ናካጎሎ፣ አግነስ ናቡኬንያ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ትዕግስት አዳነ በራሷ ላይ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ወክሎ የመሳተፍ ህልሙ ግማሽ ፍጻሜ ላይ ተገቷል።

ንግድ ባንክ ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት ይጫወታል።


የዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ለፍጻሜ አልፏል። በፍጻሜው ከኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ እና ከደቡብ ሱዳን ዬ ጆይንት ስታርስ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።

ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ እና ዬ ጆይንት ስታርስ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የግማሽ ፍጻሜ አሸናፊ ቡድኖች ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በፍጻሜው ይገናኛሉ።

የማጣሪያ ውድድሩን የሚያሸንፈው ክለብ በሻምፒዮንስ ሊጉ ሴካፋ ዞንን ወክሎ መሳተፉን ያረጋግጣል።

ነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሩዋንዳ ኪጋሊ የተጀመረው የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከነገ በስቲያ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም