ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትምህርት ጥራት፣ በቴክኖሎጂና በፈጠራ ስራዎች ራሳቸውን በማብቃት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትምህርት ጥራት፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በፈጠራ ስራዎች ራሳቸውን በማብቃት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ አስገነዘቡ።

የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ ሀገር አቀፍ የትምህርት ኮንፍረንስ እያካሄደ ይገኛል።

በኮንፍረንሱ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔን ጨምሮ የሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶች ተገኝተዋል።

ኮንፍረንሱ ለ15ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በየአመቱ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት የመፍትሄ ሃሳቦች የሚቀመጥበት መድረክ መሆኑ ተጠቅሷል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኩራ ጡሽኔ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የምክክር መድረኩ በሀገሪቱ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል፣ የምርምር ስራዎችን ለማቀናጀት ያስችላል።

መድረኩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በመማር ማስተማር እና በጥናትና ምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትብብር ላይ እያመጣ ያለውን አዎንታዊና የጎንዮሽ ተፅእኖዎች ላይ ያተኮረ መሆኑንም አንስተዋል።

በተጨማሪም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በሰው ሃይል፣ በመሰረተ ልማትና ቤሌሎች ዘርፎች ያላቸውን ዝግጁነት ላይም ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለትምህርት ጥራትን መረጋገጥ፣ ለጥናትና ምርምር ሂደት ብሎም ለመረጃ አሰባሰብና ትንተና አስተዋፅኦ እንዳለውም ገልፀዋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለሰው ልጅ እገዛ የሚያደርግ በመሆኑ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ቴክኖሎጂውን በአግባቡ በመጠቀም የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመማር ማስተማር ሂደት፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም ዩኒቨርቲዎችን የፈጠራ ማዕከል ለማድረግ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን መጠቀም አዋጪ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት ጥራት፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በፈጠራ ስራዎች ራሳቸውን በማብቃት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም