የጎቤ እና የሺኖዬ ጨዋታዎች ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ መካሄድ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የጎቤ እና የሺኖዬ ጨዋታዎች ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ መካሄድ አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሞ ባህል መሠረት በየዓመቱ በወጣቶችና ልጃገረዶች የሚካሄዱ የጎቤ እና የሺኖዬ ጨዋታዎች ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ መከናወን እንዳለባቸው የቱለማ አባ ገዳ ጌቱ ተሊላ አሳሰቡ።
ጎቤ እና ሺኖዬ በኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ውስጥ የሚከወኑ፣ የክረምት ወቅት አልፎ የጸደይ (የብራ) ወቅት መግባቱንና የዘመን መለወጫን የሚያበስሩ ታላላቅ ባህላዊ የወጣቶች ጨዋታዎች እና ትውፊቶች ናቸው።
የቱለማ አባ ገዳ ጌቱ ተሊላ ዛሬ በሆራ ፊንፊኔ የጎቤ እና የሺኖዬ ጨዋታ ባህላዊ እሴታቸውን እና ወጉን ጠብቀው በሚካሄዱበት ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በወጣቶች እና ልጃገረዶች የሚከናወኑት የጎቤ እና የሺኖዬ ጨዋታ የኦሮሞ የቀደመ ባህላዊ እሴቱንና ወጉን በጠበቀ መልኩ መካሄድ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ጎቤ እና ሺኖዬ ብራን ለመቀበል በወጣቶች እና ልጃገረዶች የሚካሄዱ ጨዋታዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጎቤ እና ሺኖዬ ጨዋታዎች ስርዓት ውስጥ ሁሉም ነገር ወግ እና ወሰን ያለው መሆኑን የገለጹት አባ ገዳው፤ ጨዋታዎቹ ለአቅመ አዳም እና ሔዋን በደረሱ ወጣቶች እና ልጃገረዶች ብቻ የሚከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በጨዋታውም ወጣቶች እና ልጃገረዶች እየተዘዋወሩ በመጨፈር ስጦታ የሚቀበሉበት እና "እንኳን ለብራ ወቅት አደረሳችሁ" የሚሉበት መሆኑን ገልጸዋል።
የጎቤ እና ሽኖዬ ጨዋታዎች ባህላዊ እሴትን እና ወጉን ጠብቀው እንዲከናወኑ የሚመለከተው አካል ሁሉ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የጎቤ እና ሽኖዬ ጨዋታዎች ከነሀሴ አጋማሽ ጀምሮ እስከ መስከረም እንደሚካሄዱ ታውቋል።