ኢትዮጵያ ከታይላንድ ጋር ያላትን ዘመናት ያስቆጠረ ወዳጅነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት አጋርነት ለመቀየር ቁርጠኛ ናት- አምባሳደር ደዋኖ ከድር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከታይላንድ ጋር ያላትን ዘመናት ያስቆጠረ ወዳጅነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት አጋርነት ለመቀየር ቁርጠኛ ናት- አምባሳደር ደዋኖ ከድር
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከታይላንድ ጋር ያላትን ዘመናት ያስቆጠረ ወዳጅነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት አጋርነት ለመቀየር ቁርጠኛ መሆኗን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያና ፓስፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ደዋኖ ከድር ገለጹ።
በኢትዮጵያ የታይላንድ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጂሩሳያ ቢራናንዳ በበኩላቸው ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና የኢኮኖሚ ትብብሯን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።
"ታይላንድ-ኢትዮጵያ፡ የቢዝነስ ግንኙነትን መገንባት" በሚል መሪ ሃሳብ የታይላንድ-ኢትዮጵያ የቢዝነስ ፎረም እየተካሄደ ነው።
በፎረሙ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የኢትዮጵያ እና የታይላንድ የንግድ ማህበረሰብ አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያና ፓስፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ደዋኖ ከድር በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ረጅም ታሪክ ያለው ነው።
ይህንን የፖለቲካ ግንኙነቱን ወደ ተጨባጭ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ማሸጋገር እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም ታይላንድ በቱሪዝም፣ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በፋርማሲዩቲካልስ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላትን የበለጸገ ልምድ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል።
በተጨማሪም ታይላንድ አዲስ ይፋ ያደረገችውን "የአፍሪካ-ታይላንድ ኢኒሼቲቭ" አድንቀው፤ ጥረቱን ወደ ተጨባጭ የድርጊት መርሃ ግብር በመቀየር ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎች ያሏት ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል።
በዚህም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ የታይላንድ ኩባንያዎች እና የንግድ ማህበረሰብ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የታይላንድ አምባሳደር ጂሩሳያ ቢራናንዳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ታይላንድ ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።
ይህን የሁለቱን ሀገራት መልካም የፖለቲካ ግንኙነት ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋርነት እና ተጨባጭ የንግድ እድሎች መቀየር ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ ቁልፍ የኢኮኖሚ ማዕከል መሆኗን ጠቁመው፤ ሀገሪቱ ያላት ሰፊና እያደገ የመጣ ገበያ፣ ስትራቴጂካዊ መገኛ፣ የበለጸገ የግብርና ሀብት፣ የልማት አጀንዳ እና እየተስፋፋ ያለው መሰረተ ልማት ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ሰፊ የእድል የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል።
ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገው አጋርነት የሥራ እድል የሚፈጥር፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር የሚያመጣ እንዲሁም ለጋራ ብልጽግና አስተዋፅኦ የሚያደርግ እንዲሆን እንደምትፈልግ አምባሳደሯ ተናግረዋል።
የንግድ ማህበረሰቡ ከዛሬው መድረክ ወዳጅነትን ወደ አጋርነት፣ አጋርነትን ደግሞ ለጋራ ብልጽግና እንዲያውል ጥሪ አቅርበዋል።