የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ እሴት እንዲጎለብት እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ እሴት እንዲጎለብት እያስቻለ ነው
ሰመራ፤ ነሀሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ እሴት እንዲጎለብት እያስቻለ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ገለጹ።
የፍትህ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ የ2018 የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአፋር ክልል አውሲ ረሱ ዞን ዱብቲ ከተማ አካሂደዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ እንደገለጹት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በህብረተሰቡ ውስጥ የመደጋገፍ እሴት እንዲጎለብት አድርጓል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማትም ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ስራዎችን አጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ በዛሬው እለትም በዱብቲ ከተማ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በከተማው ለሚገኙ አምስት አቅመ ደካማ ወገኖች አዲስ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን አመልክተዋል።
የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኀላፊ አቶ ኡመር ኑር በበኩላቸው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት አቅመ ደካሞችን ከመደገፍ በተጨማሪ ለተማሪዎቸ የትምህርት ቁሳቁስ በሟሟላት ረገድ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።
የዱብቲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሐመድ አሕመድ ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ በዱብቲ ከተማ ተገኝተው ላደረጉት በጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።
የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በእለቱ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።