ቀጥታ፡

ለውጥ እና ነውጥ፤ የአትክልተኛው ማስታወሻ የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ነገ ይመረቃል

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ) ፦ ፖለቲከኛ ግርማ ሰይፉ በባለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ የታዩትን የለውጥ ሒደቶችና የፖለቲካ ውጣ ውረዶችን የሚተነትን "ለውጥ እና ነውጥ፤ የአትክልተኛው ማስታወሻ" የተሰኘ አዲስ መጽሐፋቸውን ነገ ያስመርቃሉ።

ነገ ነሐሴ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በአድዋ ድል መታሰቢያ 9:00 ላይ የሚመረቀውን መጽሐፍ ምክንያት በማድረግ አቶ ግርማ ሰይፉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መጽሐፉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ከጸብና ከጠመንጃ መራቅ እንዳለበት ለማስገንዘብ እና የተዛቡ ትርክቶችን ለማስተካከል አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል።

መጽሐፉ የተሳካና የተሟላ የሀገረ መንግሥት ግንባታን ዕውን ለማድረግ ጠቃሚ ምክረ-ሀሳቦችን ያቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል።

ልዩነቶችና አለመግባባቶች በምክክር ብቻ መፈታት እንዳለባቸው በመግለጽ፣ የብሔራዊ ምክክርን አስፈላጊነት በአጽንኦት አንስተዋል፡፡

መጽሐፉ ወጣቶች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የዳር ተመልካች ሳይሆኑ መሪ ተዋናይ እንዲሆኑ እንደሚያስገነዝብ ገልጸው፤ ከመገፋፋት ይልቅ ሁሉም ወገን በትብብር ለመሥራት ፈቃደኛ መሆን አለበት ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በጋራና በትብብር ሲቆሙ ብቻ ፈተናዎችን መሸጋገር፣ እንዲሁም ድህነትንና ኋላቀርነትን ማሸነፍ እንደሚችሉ መጽሐፉ ማብራራቱን ተናግረዋል።

በነገው ዕለት በሚካሄደው የመጽሐፉ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

መጽሐፉ በስድስት ምዕራፎች የተከፋፈለና 270 ገጾች ያሉት መሆኑን ገልጸዋል።

በነገው ዕለት በይፋ ከተመረቀ በኋላ በሁሉም መጽሃፍት መድብሮች ለገበያ እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም