የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሴካፋ ማጣሪያ ፍጻሜ ለማለፍ ከካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሴካፋ ማጣሪያ ፍጻሜ ለማለፍ ከካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ጋር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል።
ጨዋታው ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድብ ሁለት በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሶስቱ ምድብ ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ ምክንያት ለግማሽ ፍጻሜ አልፏል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጅቡቲውን ኡጄኮን 11 ለ 0 በመርታቱ ባለው የግብ ክፍያ ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ አስችሎታል።
ንግድ ባንክ በምድቡ በካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ የ1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።
ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ በምድብ ሁለት በስድስት ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በምድብ ሁለት አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ካዌምፔ እና ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ የጨረሰው ንግድ ባንክ ዳግም በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተዋል።
ሁለቱ ክለቦች እ.አ.አ በ2024 በአዲስ አበባ በተካሄደው የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ማጣሪያ በግማሽ ፍጻሜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል።
ንግድ ባንክ በወቅቱ የማጣሪያ ውድድሩን በማሸነፍ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ኬንያ ፖሊስ ቡሌስ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የግማሽ ፍጻሜ አሸናፊ ቡድኖች ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በፍጻሜው ይገናኛሉ።
የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሩዋንዳ ኪጋሊ እየካሄደ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማጣሪያ ውድድሩን ካሸነፈ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለሁለተኛ ጊዜ መሳተፉን ያረጋግጣል።
በ2026 የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ለመሳተፍ 36 ክለቦች በስድስት አህጉራዊ ዞኖች ተከፍለው የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።
በአህጉራዊ ቀጣናዎች በሚደረጉ ማጣሪያዎች አሸናፊ የሆኑ ክለቦች፣ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ የሞሮኮው ኤኤስ ፋር እና ውድድሩን የሚያዘጋጀው ሀገር ተወካይ ጨምሮ ስምንት ቡድኖች በዋናው ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።
የ2026 የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ዋና ውድድር አዘጋጅ ሀገር በቅርቡ በአወዳዳሪው አካል ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።