በኦሮሚያ ክልል ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ድጋፋችንን እናጠናክራለን - የሃይማኖት አባቶችና አባ ገዳዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ድጋፋችንን እናጠናክራለን - የሃይማኖት አባቶችና አባ ገዳዎች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት እንደሚደግፉ የሃይማኖት አባቶችና አባ ገዳዎች ገለጹ።
በክልሉ አደጋን በራስ አቅም የመቋቋም አቅምን ለማጠናከርና የውጭ እርዳታ ጥገኝነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው።
በተለይም የተፈጥሮ ድርቅ፣ ጎርፍና ሌሎች ሰው ሠራሽ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ፈጣንና ዘላቂ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የውስጥ አቅም የመገንባት ተግባራት ተከናውነዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሃይማኖት አባቶችና አባ ገዳዎች፤ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
አደጋዎችን በራስ አቅም የመቋቋምና የወገንን ችግር በጋራ የመፍታት ባህል የሕዝቡ የቆየ እሴት በመሆኑ፤ ይህንኑ ባህል ከማጠናከር አንጻር ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም ማህበረሰቡን በማስተባበር፣ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን በማጠናከርና ሀብት በማሰባሰብ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የሸገር ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ አባ አፈወርቅ ዮሐንስ በበኩላቸው፤ ለሚከሰቱ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት ‘ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ’ ያከናወናቸው ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በማቃለል ረገድ የላቀ ሚና እንደነበረው ጠቅሰዋል።
ተቋሙ እያከናወናቸው ያሉትን ስኬታማ ተግባራት በመደገፍ በኩል የሃይማኖት ተቋማት አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የ‘ቡሳ ጎኖፋ’ ስርዓት የሚበረታታ በመሆኑ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ የሁሉም አካላት ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ በሸገር ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ሰይድ ሁሴን ናቸው።
አሰራሩ ያለምንም ልዩነት ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በግንባር ቀደምትነት የሚደግፍ በመሆኑ፣ ማንኛውም በጎ ፈቃደኛ ዜጋና ተቋም አቅሙ የፈቀደውን ያህል ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
‘ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ’ ከገዳ ስርዓት የተቀዳና የኦሮሞ ሕዝብ በደስታም ሆነ በችግር ጊዜ በጋራ የሚረዳዳበት የቆየና የዳበረ ባህላዊ እሴት መሆኑን የገለጹት ደግሞ አባ ገዳ ወርቅነህ ተሬሳ ናቸው።
ተቋሙ ለችግር የተጋለጡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍና አደጋዎችን በመቋቋም ረገድ ያከናወናቸው ተግባራት ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሆነም ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል የዲያስፖራ አባል የሆኑት አቶ ለሜሳ ከበደ በበኩላቸው፤ ‘ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ’ አደጋዎች ሲከሰቱ በራስ አቅም ለመቋቋምና በቂ ምላሽ ለመስጠት የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ይህን በራስ አቅም የመቆም ጥረት ከግብ ለማድረስም የዳያስፖራው ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።